“ግብጽን የሚያዋጣት ሕግ የሆነውን የናይል ትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ፈርሞ መቀበል ነው” – ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሪ (ዶ/ር) የታሪክ ምሁር

አዲስ አበባ፦ በአሁኑ ወቅት ግብጽን የሚያዋጣት ከወራት በፊት ተፈርሞ ሕግ የሆነውን የናይል ትብብር ማሕቀፍ ስምምነትን ፈርሞ መቀበል እንደሆነ የታሪክ ምሁር ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሬ (ዶ/ር) አስታወቁ። ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ይዛ ያለ ባሕር በር መኖር የማይታሰብ ነገር እንደሆነም አመልክተዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ አብላጫዎቹ የተፋሰሱ ሀገራት የናይል ትብብር ማሕቀፍ ስምምነትን መቀበላቸውን በፊርማቸው ከማረጋገጥም ባሻገር የሀገራቸው ሕግ አድርገው አጽድቀውታል።

የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት በስድስት የተፋሰሱ ሀገሮች በመጽደቁም ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ሕግ መሆኑን ያስታወሱት የታሪክ ምሁሩ ፤ ለግብጽም መልካም የሚሆነው ማሕቀፉን ተቀብላ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ ብትሠራ እንደሆነ አመልክተዋል። ተባብራ መሥራቷም የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋታል ብለዋል ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በኢትዮጵያ በኩል ዋናው ቁም ነገር በአቋም መጽናት ነው። የትብብር ማሕቀፉ ሥራ ላይ እንዲውል በማድረጉ በኩል አሁን የመጣችበት መንገድ መልካም የሚባል ነው፤ ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ ነው።

በኢትዮጵያ ጉዳይ አርፋ መቀመጥን የማትወደዋ ግብጽ፣ እንዲሁ ከመድከም ባለፈ ምንም ማድረግ አልቻለችም ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ፣ የትብብር ማሕቀፉን ፈርማ በማጽደቅ ተጠቃሚ ብትሆን ጥቅሙ ለእርሷ ነው ብለዋል።

የባሕር በር ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ፤ ሀገሪቱ 130 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ይዛ ያለ ባሕር በር መኖር ትችላለች ተብሎ እንደማይታሰብ ያመለከቱት የታሪክ ምሁሩ ፤ ይህ ለማንም ግልጽ የሆነ ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ግብጽ ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋ ምላሽ እንዳያገኝ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በማበር የተለያዩ ሴራዎችን ስታሴር ብትቆይም ነገሮች በፈለገችው መጠን ሊሔዱላት አልቻለም፤ ሁሌም ቢሆን የእሷ ዋና ዓላማ የዓባይ ወንዝ ነው። ኢትዮጵያ ዓባይን እንዳትነካ በመፈለጓ ብቻ ሌላ ሌላውን በማስጣል ኢትዮጵያን ለማዳከም ትሮጣለች ሲሉ ተናግረዋል።

እኛ የባሕር በር ያስፈልገናል ብለን ወስነናል። ይሁንና የባሕር በር አስፈላጊያችን ነው ስንል ማግኘት የምንፈልገው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው። ለምሳሌ የሶማሊላንድ ፈቃደኝነት ባይኖር ኖሮ ስምምነቱ ሊፈረም አይችልም ነበር። መስማማቱና መፈረሙ ትክክል ሆኖ ሳለ ይህ ለምን ተደረገ በሚል አንዳንዶች ጸብ ያለሽ በዳቦ በሚመስል አካሔድ አንዱን በሌላው ላይ ለማነሳሳት ተንቀሳቅሰዋል። ወዲህም ተሮጠ ወዲያ ኢትዮጵያ ያነሳችውን የባሕር በር ጥያቄ ስኬታማ ሳታስደርግ ከዓላማዋ ዝንፍ እንደማትል መረዳቱ ተገቢ ይመስለኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሶማሊላንድ የተደረገው የመንግሥት ለውጥ ለደረስነው ስምምነት ምንም ለውጥ የሚያመጣ አይደለም። ሁለቱም አቋማቸውን አልቀየሩም። ይህ የሚያሳየን ደግሞ ሶማሊላንድ ብሔራዊ ጥቅሟን አውቃ ፤ ብሔራዊ ጥቅሟ ከኢትዮጵያ ጋር መተሳሰብ መሆኑን ወስና እየቀጠለች መሆኑን ነው ብለዋል

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 12 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You