አዲስ አበባ፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም ዘርፍ ያሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ያካተተ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ። ይህንኑ ሥራ እንዲሠሩ በ27 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሀገር በቀል ማዕከላት ተለይተዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርትና የፕሮግራሞች ዴስክ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ነገዎ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው ሀገር በቀል ዕውቀቶች በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲካተቱ ይጠቅሳል። ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ ሳይንሳዊ ጥናት ማድረግ ከተጀመረ ሁለት ዓመታት ሆኖታል። እስካሁን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የተገኙ ግኝቶች የሚያሳዩት ሀገር በቀል ዕውቀቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ቢካተቱ ለሥራ ፈጠራና ለሳይንሳዊ ምርምር ግብዓት የሚሆኑ ናቸው።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ የተደረገው የዳሰሳ ጥናት ሰነድ ለባለሙያዎች ተሰጥቶ ከተገመገመ በኋላ ለትምህርት ሚኒስቴር ተልኳል። በቅርቡም ወደ ትምህርት ተቋማቱና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ይላካል። በግብርና፣ በጤና፣ በማህበራዊ ፍልስፍናዎችና የችግር አፈታት ዘዴዎች ላይ ሲባክኑ የኖሩ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ወደ ምርምር እንዲመጡ እየተደረገ ነው።
‹‹ሀገር በቀል ዕውቀት እንደ ልማዳዊና ኋላቀር ይታይ ነበር›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ሀገር በቀል ዕውቀትን የአሜሪካ፣ አውሮፓና እስያ ሀገራት ሁሉ ይጠቀሙበታል። በአፍሪካ ሀገራትም ብሔራዊ ስትራቴጂ አድርገው ከአንደኛ ደረጃ ጀምረው የሚጠቀሙበት አሉ ብለዋል።
ሀገር በቀል ዕውቀቶች ወደ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የሚካተቱት ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር በማጣጣምና በባለሙያዎች በመለየት መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ‹‹ባህላዊ ሐኪሞች አሉ ማለት ለመድኃኒትነት የሚጠቀሙት ጥሬ ምርት አለ ማለት ነው።ለመድኃኒትነት የተጠቀሙትን ዕፅዋት በዘመናዊው የሕክምና ሳይንስ ማጥናት እና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ማለት ነው›› ብለዋል። አርሶ አደሩ ለዘመናት ሲጠቀመው የኖረውን የግብርና ጥበብ ከሳይንሱ ጋር ማዋሃድ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ሀገር በቀል ዕውቀት በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ደረጃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደ አንድ የትምህርት ክፍል እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ ሀገር በቀል ዕውቀት ትኩረት መሰጠቱ የባለቤትነት መብት እንዲኖረው ያደርጋል ብለዋል። ኪነ ጥበብ እና ንግድን ጨምሮ በብዙ ዘርፎች የተለየው የሀገር በቀል ዕውቀቶች ጥናት፤ የባለቤትነትን መብት የጠበቀ ነው ብለዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማህበረሰብ ችግር ፈቺ ምርምር የሚሠሩ እንደመሆናቸው ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ትኩረት ይሰጣል ያሉት ኃላፊው፤ የሀገር በቀል ዕውቀቶች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12 / 2017 ዓ.ም