“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ጉዳይ ለምርጫ የሚቀርብ አይደለም” – አቶ ጥላሁን ከበደ

– አቶ ጥላሁን ከበደ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

አርባ ምንጭ ፡- በክልሉ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ሂደት ለምርጫ የሚቀርብና ለነገ የሚተው ጉዳይ እንዳልሆነ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ። በክልሉ ከ 76ሺህ በላይ ሰዎችን ከልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ለማስመረቅ መታቀዱ ተጠቁሟል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳስታወቁት ፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚለው ንቅናቄ እንደሀገር ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ሂደት ለምርጫ የሚቀርብና ለነገ የሚተው ጉዳይ አለመሆኑ ግንዛቤ ተፈጥሮበት ፣ የምግብ ሉዓላዊነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ሥራዎች ታቅደው እየተሠሩ ነው።

እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ  ፀጋዎችን የመለየት ሥራ አስቀድሞ መከናወኑን ጠቁመው፤ ክልሉ በተለይም ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች ባለቤት እንደመሆኑ ፣ይህንን ሀብት በመጠቀም ክረምት ከበጋ ከተሠራ በአጭር ጊዜ ውስጥ በምግብ እህል ራሱን የሚችልበት እድል ስለመኖሩ መግባባት መፈጠሩን አስገንዝበዋል።

የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት ሆነን ሳለ ከሌላ ሀገር በተመረተ ምርት ተመፅዋች መሆን የለብንም የሚል ቁጭት ከአመራር እስከ ሕዝቡ ድረስ ተፈጥሮ ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን ፤ እያንዳንዱ አመራር የሚመራው ክልል፣ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ተረጅ እንዳይሆን በቁጭት በመነሳት ማህበረሰቡን አስተባብሮ መሥራት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

በየትኛውም ጊዜ የሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች መቋቋም የሚያስችል አቅም መፍጠር ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካል ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራም አቶ ጥላሁን ጥሪ አቅርበዋል ። ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እና በክልሉ የሚገኙ ቤተሰቦች በምግብና በሥነ ምግብ ራሳቸውን ችለው ለሌሎች መትረፍ የሚቻልበትን መንገድ ቀይሰን መሥራት አለብን” ሲሉ ተናግረዋል

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋምአ በበኩላቸው ፤ በክልሉ በሚገኙ 52 ወረዳዎች ላይ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተው ፤ በተያዘው ዓመት ለ76 ሺ 671 ሰዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ለማስመረቅ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት በመርሃ-ግብሩ ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የምግብ ክፍተት ለመሙላት ርብርብ መደረጉንም ጠቁመው፤ ዘንድሮ በተለየ መንገድ በርካታ ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል። በዋነኝነትም የህብረተሰቡን የምግብ ክፍተት ከመሙላት ባሻገር በተመረጡ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲችሉና ከተረጅነት እንዲላቀቁ የማድረግ ሥራ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሪነት እየተከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ተጠቃሚዎቹ በግብርናም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ ሥልጠና ወስደው፣ የአዋጭነት ጥናት ተጠንቶ፣ ብድር አግኝተው እንዲሠሩና ጥሪት እንዲያፈሩ ሰፊ ሥራ ሠርተናል ብለዋል ።

በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ እያንዳንዱ ግለሰብ ጥሪቱን እንዲገነባ አቅም የሚሆኑ የማህበረሰብ ሥራዎች ትኩረት መስጠቱን አመልክተዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በተለይም ማህበረሰቡ ራሱ “ከተረጂነት መውጣት እችላለሁ” የሚል አስተሳሰብ ለመፍጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በተጨባጭ ውጤታማ እንዲሆኑ እና ከተረጅነት የሚያወጡ የቴክኖሎጂ ፣ የግብዓት፣ የብድርና መሰል ድጋፎች በተቀናጀ መልኩ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ከ76 ሺህ ሰዎች በላይ ከመርሃ ግብሩ እንዲመረቁ በማድረግ ሀገራዊውን ንቅናቄ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ በተጓዳኝም የክልሉን የምግብ ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል ።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You