የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች ከሰሞኑ ለአፍሪካ ቀንድ የተሸረበውን ሴራ ማክሸፍ ያስቻለ ስምምነት በአንካራ ተስማምተዋል። በስምምነቱም በወዳጅነት በመከባበር መንፈስ ያለፉ ልዩነቶችን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ በመተው በትብብር ለጋራ ብልፅግና እንደሚሠሩ አመላክተዋል። ስምምነቱ በተካሔደበት ወቅት በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው ለሶማሊያ መስዋእትነት ለከፈሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማሊያ ዕውቅና ሰጥታለች። ይህ ስምምነት በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ከማስፈን አንፃር አንድምታው ምንድን ነው? ስንል የተለያዩ ምሁራንን አነጋግረናል።
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ እንደሚሉት ፤ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አንድ አካል ወይም ዘመዳሞች ናቸው ማለት ይቻላል። ማንም እንደሚያውቀው የቀጣናው ሕዝብ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በኢኮኖሚ የተያያዘ ነው። ይህንን ትስስር ደግሞ በቀላሉ ቆራርጦ መጣል አይቻልም።
ነገር ግን አንዳንዴ ችግር ሊፈጠር ይችላል። የሐሰን ሼክ ምርጫና የሶማሊላንድ ስምምነት ተመሳሳይ ጊዜ ላይ በመሆኑ፤ ሐሰን ሼክ በችኮላ እና በመደነጋገር ጎረቤትነትን እና ወዳጅነትን በመዘንጋት ኢትዮጵያን መወንጀሉ ተገቢ አልነበረም። ‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል›› እንደተባለው፤ ውንጀላው ክፍተት ፈጥሮ ነበር።
ምስራቅ አፍሪካ የንግድ መሳለጫ መሆኑ፤ ጂኦ ፖለቲክሱ ከበድ የሚል ነው። አንገብጋቢ ቦታ መሆኑን ተከትሎ፤ ሁሉም ዓይኑን የሚተክልበት እና ጥቅሙን የሚያስጠብቅበት ወዳጅም ጠላትም የሚያንዣብብበት ነው የሚሉት ምሁሩ፤ በራሳችን ክፍተት ሲፈጠር፤ ያንን ክፍተት የሚያሰፋ ይመጣል ፤ ክፍተቱን ተከትሎ የግብፅ፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ ስምምነት መታየቱን አስታውሰዋል።
ነገር ግን የሶስቱ ሀገራት ስምምነት ላይ ውሃ በሚቸልስ መልኩ በቱርክ አማካኝነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ስምምነት ተደረሰ። የአንካራው ስምምነት የጦዘውን ሁኔታ ያቀዘቀዘ፣ በአፍሪካ ቀንድ የተሸረበውን ሴራ ያከሸፈ በመሆኑ እንደ ትልቅ ፀጋ መታየት አለበት ነው ያሉት።
በምንም መልኩም ቢሆን ከጦርነት ሰላም እንደሚሻል አያጠያይቅም። ትልቁ ጉዳይ ሁለቱ ሀገሮች ሰላምን መምረጣቸው ይበል የሚያሰኝ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፤ ለጊዜው ስምምነቱን በተመለከተ የሚታወቅ ዝርዝር ጉዳይ ባይኖርም ወደ ፊት በአራት ወር ውስጥ ብዙ ሥራ እንደሚሠራ ተጠቅሷል። ይህ ለኢትዮጵያም ሆነ በአጠቃላይ ለቀጣናው መልካም ዕድል ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ በኩል ከአሁን በኋላም በዲፕሎማሲው ረገድ ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ ይጠቁማሉ።
ስምምነቱ የቀጣናው ሰላም እንዲረጋገጥ፤ የነበረውን ክፍተት ለማጥበብ እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ የቱርክም ስሜት ሁሉንም ወዳጅ አድርጎ መቆየት በመሆኑ ሀገራቱን ወደ ሰላም ለማስገባት ያደረገችው ጥረት የሚበረታታ ነው ያሉት።
ስምምነቱ የበለጠ አስደሳች እንዲሆን በአካባቢው ሽማግሌ ችግር የመፍታት ጥበብ ወይም በአፍሪካ ሕብረት ቢሠራ መልካም ነበር የሚል እምነት እንዳላቸው አውስተው፤ ሆኖም ጉዳዩ ከአፍሪካ ወጥቶ ወደ ቱርክ ቢሔድም፤ ለሰላም የማይከፈል ዋጋ ስለሌለ በዛም በኩል ሆኖ በቀጣናው ሠላም መፈጠሩ እጅግ መልካም መሆኑን አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲያገለግሉ የነበሩት፤ በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ዓመት ፕሬዚዳንት ሆነው የሠሩት እና አሁን በጨፌ ኦሮሚያ የምክር ቤት አባል እና የመንግሥት በጀት እና ሀብት አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገመቹ አራርሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ጎረቤት ሀገሮች ናቸው። አንዱ ጋር ሰላም ኖሮ ሌላው ጋር ሰላም ቢጠፋ፤ ለሁለቱም ጥሩ አይመጣም። አንዱ ሰላም ማጣቱ ሌላኛውም በተለያየ መልኩ የገፈቱ ቀማሽ ያደርገዋል። ከዚህ አኳያም በቀጣናው ሰላም እና ልማት ላይ ሰፊ ትብብር ያስፈልጋል።
ይህንን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ በተለይ ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ቅድሚያ ትሰጣለች። ከጎረቤት ሀገር ጋር ብቻ ሳይሆን የሀገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም እና የጋራ ተጠቃሚነትን እንዲሁም የዜጎችን ክብር ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ከየትኛውም ሀገር ጋር ሰላማዊ የሆነ ትብብር እና የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ትከተላለች። የአንካራው ስምምነትም የዚሁ አካል ነው ይላሉ።
እንደ ገመቹ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት በ2ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት። ትልቅ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስ ፤ ከቀጣናው ቅድሚያ ይዛ የምትገኝ ሀገር ብትሆንም፤ ይህች ትልቅ ሀገር በታሪክ አጋጣሚ የባሕር በር አጥታ በር ተዘግቶባታል። በዓለም ደረጃ ምናልባትም በኢትዮጵያ ደረጃ ያሉ እና የባሕር በር የሌላቸው ሀገሮች በጣም ጥቂት ናቸው። ይህች ሀገር የባሕር በር ያስፈልገኛል ብላ መሠረታዊ ጥያቄ አቅርባለች። ይህ ደግሞ ተገቢ ጥያቄ ነው።
በዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ሕጋዊ መብት አላት። ታሪካዊ ዳራዋም ሲቃኝ ለረዥም ጊዜ የቀይ ባሕር ወደብ እንደነበራት ይታወቃል። የባሕር በሩን ያጣችው በፖለቲካ ሸፍጥ ነው። በታሪክ ኢ-ፍትሃዊነት ቢፈፀምባትም አሁን ደግሞ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በመስማማት የጋራ ጥቅምን መሠረት በማድረግ ‹‹የባሕር በር የማግኘት መብት አለኝ፤ ማግኘት ይገባኛል›› የሚል ጥያቄ አቅርባለች።
ከሶማሊላንድ ጋር የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች። ሶማሊላንድ በዓለም ደረጃ ሙሉ ዕውቅና ባይኖራትም የምታስበው ነፃ ሀገር እንደሆነች ነው። ለ30 ዓመታት ምርጫ ስታካሂድ የነበረች እና አንዳንድ ሀገሮች ጋርም ቆንፅላ ሳይቀር አላት። ሶማሊያ ደግሞ ‹‹ሶማሊላንድ የእኔ ግዛት ናት ከእርሷ ጋር የተነጠለ ግንኙነት መፍጠር የእኔን ሉዓላዊነት መንካት ነው ።›› ብላለች። በዚህ ምክንያት ሁለቱ ሀገሮች ወደ ማይሆን እሰጣ ገባ ውስጥ እንዳይገቡ በማሰብ በቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን አማካኝነት በአንካራ ስምምነት ተደርጓል።
በእርግጥ ኢትዮጵያ የማንንም ሀገር ሉዓላዊነት የመጣስ ፍላጎት የላትም። ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በታሪኳም ኢትዮጵያ የማንንም ድንበር ጥሳ አታውቅም። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውም ተመሳሳይ አቋም ያለው ነው። የሶማሊያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ የባሕር በር የምታገኝበት እና እነዚህ ሁለቱ ሀገሮች ደግሞ በሰላም መኖር የሚችሉበትን ስምምነት ተፈራርመዋል። የሁለቱ ሀገራት ሠላማዊ ግንኙነት ደግሞ ቀጣናው ላይ ሰላም እንዲሰፍንና በቀጣናው ተደግሶ የነበረው የቀውስ ሴራ እንዲከሽፍ ማድረጉን ነው ያመለከቱት።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም