ከተሞቹ ምርትን መደበቅና ያለደረሰኝ ግብይትን ለመከላከል በጋራ እየሠሩ ነው

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተሞች ምርትን መደበቅ፤ ያለደረሰኝ ግብይት ማከናወንና መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል በጋራ እየሠሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገለጸ፡፡ በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች የሚፈፀም የኢኮኖሚ አሻጥር ወንጀልን በቅንጅት ለመከላከል የስምምነት ፊርማ ትናንት ተፈራርመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባና በሸገር ከተሞች የሚፈፀሙ የኢኮኖሚ አሻጥር ወንጀሎችን ማለትም ምርትን መደበቅ፤ ያለደረሰኝ ግብይት ማከናወን፤ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅሎ ለገበያ ማቅረብና መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል የፀጥታ አካላት በጋራ እየሠሩ ነው፡፡ ስምምነቱም የኢኮኖሚ አሻጥር ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ እና የሸገር ከተማ የሰላምና የፀጥታ ቢሮዎች እየሠሩት ባለው ሰላምና ፀጥታን የማስከበር ሥራ በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ የሚፈፀሙ የአሻጥር ወንጀሎችን ምጣኔም መቀነስ መቻሉን አመልክተው፤ እየተሠራ ያለው ቅንጅታዊ ሥራ ቅርፃቸውንና ይዘታቸውን እየቀያየሩ ለሚፈፀሙ የኢኮኖሚ ወንጀሎችን ለመከላከል እያስቻለ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ስምምነቱም ቅንጅታዊ አሠራሩን ይበልጥ በማጠናከር ከአዲስ አበባ ወደ ሸገር፤ ከሸገር ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተዘዋወሩ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑ ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ከተማዎች እየተሠሩ ያሉ ሰላምና ፀጥታን የማስከበር ሥራ የአዳባባይ በዓላትና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሂዱ አስችሏል ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ፤ መዲናዋ ትልልቅ ኢኮኖሚዎች የሚንቀሳቀሱባት፤ ዲፕሎማቶች የሚኖሩባትና የቱሪስት ፍስት ያለባት ከተማ እንደመሆኗ ይህን የሚመጥን ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ወንጀሎችን ከምንጫቸው ለማድረቅም በሁለቱ ከተማዎች ሕዝብን ከሕዝብ የማገናኘትና የሰላም ባለቤት የማድረግ ሥራ ይሠራል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ሕዝብን የሰላም ባለቤት በማድረግ፤ ከሸገር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጉዮ ገልገሎ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የኢኮኖሚ አሻጥር ወንጀሎችን በቅንጅት ለመከላከል ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

በሁለቱ ከተሞች በቅንጅት እየተሠራ ያለው ሰላምና ፀጥታን የማስከበር ሥራ የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ማድረግ አስችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የንግድ እንቅስቃሴን፤ የኢኮኖሚ እድገትን ለማሳለጥና ዜጎች ምቹ ሕይወት እንዲኖሩ ሰላም አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ ጉዮ፤ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስቀጠልና የዜጎችን በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

 አዲስ ዘመን ታህሳስ 11 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You