የመገናኛ ብዙሃን ሚና በሀገራዊ ምክክሩ

ዜና ሀተታ

ከተቋቋመ ሶስተኛ ዓመቱን ሊያስቆጥር ሁለት ወራቶች የቀሩት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን በነበረው ቆይታ ምክክሩን ለመጀመር መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም የተለያዩ ሂደቶችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ሂደቶች አንስቶ እስከ ምክክሩ መጠናቀቂያ ድረስ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምን መሆን አለበት በሚለው ዙሪያ የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከዩኤንዲፒ ጋር በመተባበር የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

በውይይት መድረኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አብዲሳ ዘርአይ (ዶ/ር) በበኩላቸው በምክክር ሂደቱ ለመገናኛ ብዙሃን ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ያነሳሉ፡፡

መገናኛ ብዙሃን በተለያዩ ፅንፎች የመወሰድ፣ የተለያዩ አካላት ፍላጎት ማንፀባረቂያ መሆን፣ የባለሙያዎቻቸውን ደህንነት አለመጠበቅ እንዲሁም የባለሙያዎቻቸው ልምድ ማነስ በተለይም ሀገራዊ ምክክር እንዴት እንደሚዘገብ አለማወቅ ተግዳሮቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡

መገናኛ ብዙሃን እንደተቋም የራሳቸውን አጀንዳ ማስያዝ እንዳለባቸው የጠቆሙት መምህሩ፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን ከተጠቀሙበት አዎንታዊ ሚና የመጫወት እድል እንዳላቸው ይጠቁማሉ፡፡ በሂደቱም መገናኛ ብዙሃን ማህበረሰባዊ መተማመንን የሚሸረሽሩ ቁስሎችን የማሻር ሚና እንደሚኖራቸው ነው የገለጹት፡፡ ይህም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ጉልህ ሚና የሚጫወቱበትን ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ወንድሙ ለገሰ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ የመገናኛ ብዙሃን ዋነኛ ሥራ ማስተማር፣ ማዝናናትና መረጃ መስጠት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ መገናኛ ብዙሃኑ ማህበረሰቡን ወደ አንድ ለማምጣትና አካታች ለማድረግ ሲነሱ የተለያዩ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ መሥራት አለባቸው፡፡

የመጀመሪያው የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ታሪክ ላይ መሥራት ነው የሚሉት መምህሩ፤ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚ ላይም ማህበረሰቡን እኩል ተሳታፊ ባደረገ መልኩ መሥራት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር መገናኛ ብዙሃን ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ መሆን እንደሚገባቸውም ያነሳሉ፡፡በተጨማሪም የዘር፣ ሃይማኖትና የጾታ ጉዳዮች ላይ አድሎአዊ ባልሆነ መልኩ መሥራት እንዳለባቸው የጠቆሙት መምህሩ፤ ሚዲያው ሁሉንም ማህበረሰብ አንድ የሚያደርግ ሥራ መሥራት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡

በተለይም ማህበራዊ ሚዲያ በጥሩ ከተጠቀምንበት ጥሩ ጥቅም እንዳለው የሚገልፁት መምህሩ፤ ብዙ ከፋፋይ ነገሮች እየተሠሩበት እንዳለና በዚህ ልክ ወደ አንድ የሚያመጡን ጉዳዮች ላይ ብንሠራበት የተሻለ ይሆናል ይላሉ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ወዘሪት ሕይወት ዮሐንስ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን ሠብዓዊ መብቶች፣ መልካም አስተዳደርና ሰላም ግንባታ ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው ያስረዳሉ፡፡

ሠብዓዊ መብትን በተመለከተ በተለይም ግጭት ያለባቸው አካባቢዎች ለሚኖር ማህበረሰብ ሠብዓዊ መብቶቹ ምን ምን እንደሆኑ ግንዛቤ የሚፈጥሩለት መገናኛ ብዙሃን ሊኖሩ ይገባል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች መገናኛ ብዙሃን የምርመራ ጋዜጠኝነትን ታሳቢ ያደረገ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡

መገናኛ ብዙሃኑ ነፃና ገለልተኛ ከመሆን አኳያ ራሳቸውን ሊፈትሹ እንደሚገባም ጠቁመው ፤አነስተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸውንና ለግጭት ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን ማካተት እንዳለባቸው ይገልፃሉ፡፡

መገናኛ ብዙሃንና መልካም አስተዳደርን በተመለከተም መገናኛ ብዙሃን መብትና ግዴታውን አውቆ የሚሞግት ማህበረሰብ ማብቃት አለባቸው ይላሉ፡፡ በተጨማሪም በኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ቃል የገቡአቸውን ጉዳዮች ስለመፈፀማቸው የማረጋገጥ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡

መገናኛ ብዙሃን ግጭት አቀጣጣይ የሆኑ ቃላቶች ላይ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ የሚገልፁት መምህሯ፤ የሰላም ግንባታ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸው ያስረዳሉ፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከሁሉም በፊት የሀገራዊ ምክክርን ፅንሰ ሃሳብ ማወቅ አለባቸው የሚሉት ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህሩ ለገሰ በላይ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

እንደእርሳቸው አባባል ጋዜጠኛው ይህ የሀገራዊ ምክክር ሂደት ከሌሎች የግጭት መፍቻ ሂደቶች በምን ይለያል የሚለውን ማወቅ አለበት፡፡ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን እንደ ድርድርና እንደ ሽምግልና እየቆጠረ ላለው ማህበረሰብም ማሳወቅ አለበት ይላሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር ግጭቱን ከሚያባብሱ ይልቅ የሚቀንሱ ዘገባዎችን መሥራት እንደሚኖርበትም ይጠቁማሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ የመረጃ ምንጮቻችን ሁልጊዜ የመንግሥት አካላት ብቻ ከሆኑ አካታችነትን ማረጋገጥ አንችልም፡፡ በተለይም ከቋንቋ አጠቃቀም አኳያ እነሱ እና እኛ የሚባል ነገር አሁንም ድረስ እንዳለ ጠቁመው፤ ይህ ድርጊት የታሰበውን ዓላማ እንዳያደናቅፍ ስጋት አለኝ ይላሉ፡፡

የግጭት መንስኤዎችን ከስር መሠረቱ ነቅሶ ለውይይት ማምጣት እንዳለበት እንዲሁም የማህበረሰቡን አመኔታ ማግኘት እንደሚኖርበትም ያብራራሉ፡፡

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 11 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You