አዲስ አበባ፡- ላኪዎች በቀጣይ ጠንካራ ውድድር እንደሚጠብቃቸው ተረድተው እራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳኦ አብዲ አሳሰቡ። በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ዙሪያ የተደረገ ጥናት ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡
አቶ ኤዳኦ አብዲ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች እና የምርት ሂደት ላይ እያጋጠሙ ስላሉ ማነቆዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት እንደገለጹት፤ በውጭ ንግድ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ባለሀብቶች/ላኪዎች ተወዳዳሪ ለመሆን እራሳቸውን በሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ በማብቃት የሚልኩት ምርቶች ላይ እሴት ሊጨምሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከውጭ የሚገቡ ባለሀብቶች በቂ የሆነ የፋይናንስ፤ የመዳረሻ ቦታ፤ የመረጃ እና የሰው ሃይል ያላቸው ስለሆኑ ለኢትዮጵያ ላኪዎች መረጃን ከማዳረስ አኳያ በጎ ሚና ይኖራቸዋል ያሉት አቶ ኤዳኦ፤ ኢትዮጵያውያኑ ባለሀብቶች በእነሱ ልክ የገበያ መዳረሻ እና የሽያጭ አቅም እንደሌላቸው አመልክተዋል።
የወጪ ንግድ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ መሆኑን ጠቁመው፤ ማህበሩም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እና የውጭ ንግዱ እንዲሳለጥ ከጂ አይ ዜድ ጋር በመተባበር ጥናት ማስጠናቱን አስታውቀዋል፡፡
ጥናቱ ከፋይናንስ፤ ከሎጂስቲክስ፤ ከፖሊሲ፤ ከገበያ እና ከንግድ ትስስር አንጻር በሀገሪቱ ያሉ አስቻይ ሁኔታዎች እና ማነቆዎች በዝርዝር ማስቀመጡን አመልክተው፤ የውይይቱም ዓላማም ባለድርሻ አካላት በጥናት በተደገፉ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረው ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ እንዲሠሩ ለማድረግ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በጥናቱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፤ የግብርና ሚኒስቴር ፤ የላኪዎቹ ሚና እና በአጠቃላይ ዘርፉ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ተቋማት ምን ማድረግ አለባቸው የሚለውን በዝርዝር የተመለከተ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
ጥናቱን ያቀረቡት የኢንቨስት ኮንሰልት ጀነራል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ተመስገን ተስፉ በበኩላቸው፤ በጥናቱ ለዘርፉ ማነቆ ናቸው ተብለው የተለዩት ጉዳዮች ከፖሊሲና ከሕግ ጋር የተያያዙ፤ ከፖሊሲ ውጭ በመንግሥት ሴክተር የሚስተዋሉ እና አተገባበር (ኦፕሬሽናል) የሆኑ ተብለው በሶስት የተከፈሉ ናቸው፡፡
ጥናቱ የተሠራው ከጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪ ማህበር አባላት እና ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ከተሰበሰቡ መረጃዎች መሆኑን ገልጸው፤ ጥናቱ አሁን ገበያው ላይ ለሚሳተፉ እና አዳዲስ ለሚመጡ ነጋዴዎች ንግዱ ላይ ያለውን ከባቢያዊ ሁኔታ በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱም ከተሳታፊ ባለድርሻ አካላት ከተነሱ ችግሮች መካከል ፤ ለላኪዎች ብቁ የሆነ እገዛ ከሴክተር መሥሪያ ቤቶች አለማግኘት፤ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ለማምረት መሬት ለማግኘት የሚወስደው ጊዜ መርዘም፤ በፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ አቅርቦት እጥረት ፤ የጸጥታ ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች የሚጠየቀው የትራንስፖርት ክፍያ ከፍተኛ መሆን እና ልውጠ ህያዋን (ጂኤምኦ ሰርተፍኬት) ለማግኘት ያለው ሂደት በዋንኛነት ተጠቃሽ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11 2017 ዓ.ም