ለአትሌቲክሱ ማን ምን ሊሠራ አቀደ?

ዜና ሐተታ

አትሌቲክስ የኢትዮጵያ ኩራትና መገለጫ ነው። የኢትዮጵያውያን አልሸነፍ ባይነትና ወኔ በዓለም አደባባይ የሚገለጥበት፣ እልፍ ጀግኖች ለሰንደቅ ዓላማ ክብር የሚዋደቁበት በመሆኑም ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከስፖርትም የዘለለ ትርጉም አለው። ስፖርቱ በዚህ ደረጃ ዋጋ እንዲሰጠውም ብርቅዬ አትሌቶች ለዘመናት ድል ችቦ እየተቀባበሉ አሁን ድረስ ዘልቀዋል።

ያም ሆኖ ስፖርቱ በየጊዜው የሚገጥሙት አስተዳደራዊ እንቅፋቶች ሀገርን በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ውጤት እንዲቀዛቀዝ ከማድረጉ በተጨማሪ ስፖርቱ ወደ ባሰ ችግር ሲያመራ ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ታዝበናል። ስፖርቱ በብዙ አስተዳደራዊ  ችግሮች ውስጥ በተዘፈቀበት በዚህ ወቅት ፌዴሬሽኑን በቀጣይ አራት ዓመታት በመሪነት የሚያገለግሉ ግለሰቦች ይመረጣሉ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 28ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ዛሬና ነገ ሲያካሂድ፣ ጉባዔው የፌዴሬሽኑን ፕሬዚዳንት ጨምሮ የሥራ ዘመኑን ያጠናቀቀውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአዳዲስ አመራሮች ይተካል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ስፖርቱን ለመምራት በምርጫው እጩ ሆነው የቀረቡ ግለሰቦች የምረጡኝ ዘመቻ ተጧጡፏል፡፡ አትሌቲክሱን ካለበት ችግር ማውጣት የሚችል ትክክለኛውን ሰው ዘንድሮም ላያገኝ እንደሚችል ስጋቶች ባንዣበቡበት ምርጫ ተስፋ ሰጪ ነገሮችም አልታጡም።

ከዚህ ቀደም ስፖርቱን ለመምራት በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ መራጮች የእጩዎችን ማንነት ጠለቅ ብለው ሳያውቁና ሳይመረምሩ ድምፅ የሚሰጡበት ሁኔታ አትሌቲክሱ አሁን ለሚገኝበት ችግር አንዱ ምክንያት ነው። ዘንድሮ በተለይም ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ እጩዎች ቀደም ብለው የምረጡኝ ቅስቀሳዎችንና በስፖርቱ ለመሥራት የሚያስቡትን እቅዶች በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ሲያቀርቡ ሰንብተዋል። ይህም መራጮች ለማን ድምፅ መስጠት እንዳለባቸው በቂ ጊዜና ግንዛቤ እንዲያገኙ እድል ይፈጥራል ተብሎ ታምኖበታል።

ከፕሬዚዳንታዊ እጩዎቹ መካከል የቀድሞው ውጤታማ አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም ትግራይ ክልልን ወክሎ ይወዳደራል። ከ2003-2007 ዓ.ም የአትሌቶች ተወካይና ከ2009- 2013 ዓ፣ም ደግሞ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገለው ገብረእግዚያብሔር ወደ ፌዴሬሽኑ አመራርነት ለመመለስ ሲወስን በስፖርቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል መሆኑን ይናገራል። በርካታ ጀግና አትሌቶችን ያፈራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሁን ያለበት ሁኔታ የማይመጥነው በመሆኑ በፕሬዚዳንትነት ቢመረጥ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለመምራት እቅድ እንዳለውም ያስረዳል።

ከእቅዶቹም መካከል በተለይ ሕግና ደንብን አክብሮ ለመሥራት ትኩረት ያደረጉ ሥራዎችን ለማከናወን መዘጋጀቱን በመጠቆምም፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን የአትሌቲክስ ነባራዊ ሁኔታ መከተል አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል። የስፖርት ቤተሰቡ ያዘነበትን የአትሌቲክስ ውጤት መመለስ፣ ከሥልጠና ጋር በተያያዘ የሚታየውን ቅሬታ መፍታት፣ ውድድሮችን ማዘመን፣ ለአትሌቶች መለማመጃ የሚሆኑ የማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በመገንባት ሰፊ እቅዶችን ይዞ ለፕሬዚዳንትነት ይወዳደራል፡፡ ለነዚህ ዕቅዶቹ መሳካትም ከባለሙያዎች ጋር በቅርበት መሥራት ቀዳሚው ጉዳይ መሆኑንና ቀድሞ በሥራ አስፈጻሚነት ተቋሙን ባገለገለበት ወቅት ተግባራዊ ያልሆኑ በርካታ ጉዳዮችን ወደ መሬት ለማውረድ የተሻለ አቅም ይዞ መመለሱን ገልጿል።

የአማራ ክልል ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው እጩ አድርጎ የወከላቸው የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያየህ አዲስ በበኩላቸው፣ አትሌቲክስ የኢትዮጵያ መገለጫ ሆኖ ሳለ በሚጠበቀው ልክ ከጊዜው ጋር ማደግ አለመቻሉ በስፖርቱ ያላቸውን ልምድና ዕውቀት ተጠቅመው ለማገልገል እንዳነሳሳቸው ያስረዳሉ። አቶ ያየህ በክልሉ የስፖርት ኮሚሽነር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ ስፖርቱ ቀደም ሲል የነበረበትንና አሁን ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ በማጤን በቀጣይ ምን መደረግ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ራዕይ አስቀምጠው ፌዴሬሽኑን ለመምራት እንደሚወዳደሩ ተናግረዋል። በፌዴሬሽኑ ውስጥ ሪፎርም በመሥራትና ሊሳኩ የሚችሉ ፖሊሲዎችን በማውጣት ስፖርቱን  በሥርዓት ለመምራት የሚያስችል አቅም እንዳላቸውም አብራርተዋል።

እንደ አቶ ያየህ ገለፃ፣ ከተመረጡ በአጭር መካከለኛና ረጅም ጊዜ የሚሳኩ እቅዶችን አዘጋጅተዋል። ቀዳሚው ጉዳይ ስፖርቱን ሊያሳድግ በሚችል ብቃት ያለ አድሎ ፌዴሬሽኑን መምራትም ትኩረታቸው ነው፡፡ በውጤት መጥፋት ያዘነውን ሕዝብ ለመካስ የሚያስችል የ100 ቀናት እቅድም አዘጋጅዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተከፋፈለውን ባለሙያ በአንድነት እንዲሠራ የሚያስችል አሠራር መፍጠር፣ ምርጥ አትሌቶችን አሰባስቦ ወደ ሥልጠና በማስገባት ለውጤት መሥራት፣ ነባሩን የአትሌቲክስ ባህል መመለስም ትኩረት ከሚሰጧቸው ጉዳዮች ቀዳሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ስፖርቱ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ከተቋማቱ ጋር በቅንጅት መሥራት፣ አትሌቶችና ሌሎች ባለሙያዎች የሚገባቸውን ማበረታቻ መስጠት፣ ጥፋት የሚፈጽሙትን ሥርዓት ማስያዝ፣ በውጪ ስፖንሰሮች ላይ የተመሰረተውን ሀብት አሰባሰብ ከባለሀብቶች ጋር በመሆን በሀገር ውስጥ እንዲያድግ ማድረግና በአግባቡ ማስተዳደር፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ የተጠናከረ የምልመላ፣ የሥልጠናና ውድድር ሥርዓት መዘርጋት፣ የአትሌቶች የህክምና ማዕከል ማቋቋም፣ ፌዴሬሽኑ ከተቋማት ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ በትብብር የሚሠራበትን ሁኔታ ማመቻቸት በረጅም ጊዜ ዕቅዶቻቸው ትኩረት የሚያደርጉባቸው ጉዳዮች እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ወክለው ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት አቶ ዱቤ ጂሎ፣ ከአትሌትነት እስከ ስፖርት ከፍተኛ አመራርነት ለረጅም ዓመታት በዘርፉ አገልግለዋል። በቴክኒክ ባለሙያነት ያገለገሉትን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሁን ደግሞ በአመራርነት በማገልገል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት እንደሚወዳደሩ የገለፁት አቶ ዱቤ፣ ከፌዴሬሽኑ ለቀው የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ከተሾሙ በኋላ የተካሄዱ ሶስት ኦሊምፒኮች (የሪዮ፣ ቶኪዮ እና ፓሪስ) የተመዘገቡ አሳፋሪ ውጤቶች እና እሱን ተከትሎ የተፈጠሩ ውዝግቦች ቁጭት ፈጥረውባቸው ፌዴሬሽኑን ለመምራት ወደ ውድድር እንደመጡም ያስታውሳሉ። አትሌቲክስ የኢትዮጵያ መለያ እንደመሆኑ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ የሚያስችል ልምድና የትምህርት ዝግጅት ያላቸውና በዓለም አቀፉ ተቋም ምርጥ ቴክኒካል ዳሬክተርነት እውቅና ያገኙ መሆናቸውም የስፖርቱን ችግር ለመፍታት እንደሚያስችላቸው ይናገራሉ።

“የሥራ ዘመኑን ያጠናቀቀው ሥራ አስፈጻሚ የታየበት መፈረካከስና እርስ በእርስ አለመስማማት፣ የቴክኒክ ኮሚቴው አሠራር እንዲሁም አደረጃጀቱን ለማረም የሚያስችል ዕቅድ ነድፌያለሁ” የሚሉት አቶ ዱቤ፣ ቀዳሚው ሥራቸውም ከፍተኛ ክፍተት የሚታይበትን የፌዴሬሽኑን ጽህፈት ቤት በተገቢው ባለሙያ ማደራጀትና ውድድር የሚመሩና የቴክኒክ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ሙያዊ ኮሚቴዎችን ማደራጀት መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ሀገር እንደመሆኗ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማዘጋጀት ቢገባትም የስፖርት መሠረተ ልማቶች አለመኖር ወደ ኋላ አስቀርቷታልም ይላሉ። ይህም አትሌቶች ልምምድ የሚያደርጉበትን ቦታ እንኳን አሳጥቷል ባይ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከዓለም አትሌቲክስ እና ሌሎች አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በአስቸኳይ የመሮጫ መም ለማስገንባት ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

ከሴቶች ተሳትፎ አንጻር በተለይ በአሠልጣኝነት በማብቃትና የታዳጊ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት ላይም ትኩረት ለማድረግ እንደሚሠሩም አክለዋል። ከምርጫው ጋር ተያይዞም ድምጽ የሚሰጡ የጉባዔው አባላት ግለሰብን ሳይሆን ሀገርን በመመልከት ለስፖርቱ ተገቢውን ሰው መምረጥ እንዳለባቸውም አቶ ዱቤ አደራ ብለዋል።

በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፉክክሩ እጩ ሆነው ከቀረቡና የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው መካከል የኦሮሚያ ክልልን የወከለው የቀድሞው ጀግና አትሌት ስለሺ ስህን ዋነኛው ነው። የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበርን በፕሬዚዳንትነት ያገለገለው ስለሺ ፌዴሬሽኑን ለመምራት ምን እቅድ እንዳለው ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 11 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You