የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ለሀገር ውስጥ ባንኮች ዕድል ወይስ ስጋት?

ዜና ትንታኔ

በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ከተጀመረ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ አለው። በእነዚህ ጊዜያትም ያጋጠሙትን መልካም እድሎች እና ፈተናዎች ተሻግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል። የዛሬ ቁመናውም ቢሆን የእድሜውን ያህል እንዳልሆነ በዘርፉ የተሠማሩ ምሁራን ይናገራሉ።

ይህንን እውነታ ለመለወጥ መንግሥት የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ የሚያስችል አዋጅ አርቅቆ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ እንዲጸድቅ አድርጓል። የሕጉ መጽደቅ በብዙ የሚጠበቅ ቢሆንም፤ አሁንም ዜጎችም ሆነ በመስኩ የሚገኙ ምሁራን የመነጋገሪያ አጀንዳ እንደሆነ ነው።

የውጭ ባለሀብቶች በባንክ ዘርፍ እንዲሠማሩ የሚፈቅደው አዋጅ ለሀገር ውስጥ ባንኮች ምን ይዞ ይመጣል፤ ተስፋ ወይስ ስጋት? በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው ጠቀሜታስ ምን ይመስላል በሚለው ሃሳብ ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

አቶ ክቡር ገና ይባላሉ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ናቸው። አዋጁ መጽደቁ የውጭ ባንኮች ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ የሚጋብዝ መሆኑን፤ ባንኮቹ ሊሠሩ የሚችሉትንና የማይችሉትን በዝርዝር ማስቀመጡን ይናገራሉ፡፡ የአዋጁ አቀራረብ ባንኮቹ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ሊያደርግ የሚችል ነው ወይስ አይደለም የሚለው ወደፊት ተግባራዊ ሲሆን የሚታይ ነው፡፡ የለውጡ ሂደት አንዱ አካል ስለሆነ ግን አዋጅ መውጣቱ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡

የአዋጁ ይዘት አቅጣጫ ገና ግልጽ ሆኖ አልተቀመጠም የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ አንዳንድ ነገሮቹ ወደፊት የሚታዩ ሆነው፤ ባለበት ሁኔታ ስናየው የውጭ ባንኮችን ለመሳብ በር የመክፈቱን ያህል፤ በባንኮቹ አሠራር ላይ ገደብ የጣሉ ይዘቶች ስላሉት፤ እነዚህ ይዘቶች ማነቆዎች እንዳይሆኑ ስጋት መኖሩን ይናገራሉ፡፡

የውጪ ባንኮቹ አዋጁን ተከትለው ወደ ሀገር ውስጥ ይመጣሉ ወይ አንዱ ጥያቄ ነው የሚሉት አቶ ክቡር ገና፤ አዋጁ እንዲመጡ ታስቦ የተዘጋጀ በመሆኑ ይመጣሉ የሚል እምነት አለ። ቢመጡም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባንኮች አብዛኛዎቹ በአማካይ ከ20 ዓመት በላይ እድሜ የሆናቸው ስለሆነ በቆዩባቸው ዓመታት ውስጥ በርካታ ለውጥ አሳይተዋል፡፡ ባንኮቹ ቢመጡም ለመወዳደር የሚያስቸግራቸው አይመስለኝም። ቴክኖሎጂውንም ገዝተው ማምጣት፤ በዘርፉ እውቀትና ልምድ ያላቸውን ሰዎች ቀጥሮ ማሠራት ይችላሉ ብለዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ኃይለመስቀል ጋዙ በበኩላቸው፤ ሌላ ሀገር ያለው የባንክ አሠራርና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የባንክ አሠራር ባህሉ አንድ አይነት ባለመሆኑ፤ የውጭ ባንኮች ጫና ሊፈጥርባቸው ይችላል ይላሉ፡፡ ችግሩ የባንክ አስተዳደሩን በተወሰነ መልኩ ሊፈትን ስለሚችል ለመግባትም ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

በዘርፉ ምርጥ ተሞክሮ ያላት ህንድ ስትሆን 46 የሚደርሱ የውጭ ባንኮችን በመያዝ የባንክ ኢንዱስትሪውን በስፋት የገነባች ሀገር ናት፡፡ የሀገሪቱ ተሞክሮ አዋጁ ከመጽደቁ ባሻገር ወደ ተግባር እንዲገባ ማድረግ እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡ በጎጥና በብሔር የተደራጁ ባንኮች ወደ አንድ ሊመጡ የሚችሉበት ዕድልን ይፈጥራል፡፡ ይህም ሆኖ የሀገር ውስጥ ባንኮች መዋሃድ ካልቻሉ  ምን አልባትም ፈተና ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ክቡር በበኩላቸው፤ የውጪ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ከጥቅሙ ባሻገር ስጋት እንዳለው ይናገራሉ። የውጭ ባንኮች ጠቅላላ ገበያውን ከተቆጣጠሩት የሀገሪቷን የወደፊት አቅጣጫ የሚመሩት እነሱ ሊሆኑ የሚችሉበት መንገድ ሰፊ ይሆናል፡፡ ለዚህም አፍሪካ ውስጥ ፈጽሞ የሀገር ውስጥ ባንክ የሌለባቸውን ፤ በውጭ ባንኮች የተዋጡ ሀገራትን በዋቢነት ይጠቅሳሉ፡፡ የውጭ ባንኮች ዋና ፍላጎት በሀገር ውስጥ ልማት ማምጣት ሳይሆን ለባለቤቶቹ እና ለባለአክሲዮኖቹ ትርፍ ማሳደግ ዓላማቸው ነው። ከልማት ይልቅ በተለይም ለውጭ ገበያ ሊቀርቡ በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡

በሌላ መልኩ ባንኮቹ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የሀገር ውስጥ ባንኮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ የሚያብራሩት አቶ ክቡር፤ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየጊዜው ቴክኖሎጂን በመቀበልና በማዋሃድ ዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመሥራት መቻሉን በመጥቀስ ባንኮች ከዚህ ተምረው ለመወዳደር ምንም የሚያስቸግራቸው ነገር አይኖርም ባይ ናቸው፡፡

ባንኮቻችን ከስጋት ይልቅ ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ የገበያው አቅም፤ ንግዱ እና ኢንዱስትሪው የት አካባቢ እንደሚንቀሳቀስ ከማንኛውም የውጭ ባንክ የበለጠ መረጃ ስላላቸው ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ፡፡ የነሱ መምጣት ሊያሳስብ አይገባም፤ ፖሊሲውም ይህን ለመከላከል ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎች መኖራቸውን መመልከትም ተገቢ እንደሆነ ይመክራሉ፡፡

አቶ ክቡር፤ የጸደቀው አዋጅ በአንድ በኩል ወደ ‹‹ሊብራሊዝም›› አልሄደም፤ ወይም ‹‹ዲቨሎፕመንታሊስት›› ወደሚባለው በመሄድ ባንኮችን ለመምራት፤ ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ የሚፈልግ ሆኖ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ገበያው የበለጠ ሚና እንዲኖረው ይፈለጋል፡፡ ስለዚህ አቅጣጫው ገና አልተለየም ብለዋል፡፡ የመንግሥት አቅጣጫ የትኛውን እንደሚከተል ገና በግልጽ አልተቀመጠም። ወደ ፊት በገበያው ከመመራት ይልቅ በዕቅድ ለመመራት ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡

አዋጁ ግቡን እንዲመታና ሀገርን በኢኮኖሚ ለማሳደግ ውጤታማ የሆኑ ሀገራትን ተሞክሮ መውሰድ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ክቡር፤ ባጭር ጊዜ ውስጥ ዕድገት ያሳዩ እንደ ቻይና፤ ጃፓን ቬትናም የመሳሰሉ ሀገራትን አሁን ለደረሱበት የዕድገት ደረጃ ሊደርሱ የቻሉት ገበያው እንዲመራ በማድረግ ብቻ ሳይሆን የለውጥ አቅጣጫው ጭምር በማስቀመጥ ነው፡፡ ዘርፉ እንዲያድግ መንግሥት ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚኖርበትም መክረዋል።

ገበያው ይምራው ከተባለ ዕድገቱ ፎቅ በመገንባት ላይ የተገነባ ይሆናል የሚሉት አቶ ክቡር፤ ከሌሎች ሀገራት እንማር ከተባለ መንግሥት ከፍተኛ የመምራት ኃላፊነት ወስዶ ሀገር ለማሳደግ የሚያስችል መንገዶችን በር በመክፈት ለዕድገት መንቀሳቀስ ይገባዋል ይላሉ፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ኃይለመስቀል ጋዙ በበኩላቸው፤ አዋጁ መጽደቁ አንድ ለሀገር እድገት መሠረት የሆነ ታሪካዊ ሁነት ነው። ተሳክቶ ባንኮች ከገቡ ለዘርፉ ብዙ ጥቅሞችን ይዘው ይመጣሉ፡፡ ከጥቅሞቹ መካከልም ባንኮቹ ሲገቡ ያደገ ቴክኖሎጂ እና የባንክ የአሠራር ሥርዓት ይዘው ይመጣሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ኢትዮ ቴሌኮም ተወዳዳሪ አለመኖሩ የኔትወርክና ኢንተርኔት ተደራሽነቱ አለመዘመኑ እንደ ቅሬታ ይነሳበት እንደነበር ያስታወሱት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ የሳፋሪኮም ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ለመወዳደር ሲል እንደ ቴሌብር የመሳሰሉ መተግባሪያዎችን በማበልጸግ መሻሻል አሳይቷል፡፡ የውጭ ባንኮች መግባትም በዘርፉ ያለውን ውድድር በማሳደግ አገልግሎቱ እዲሻሻል ያደርጋል። የሀገር ውስጥ ባንኮች ባንክ በሌለባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ገብተው የመሥራት መነቃቃት እንዲፈጥሩ ያነሳሳቸዋል ብለዋል፡፡

የሕጉ መጽደቅ እንደ ሀገር የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ለመግባት (access to global financial system) ዕድል እንደሚሰጥ የሚያብራሩት አቶ ኃይልመስቀል፤ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ያፋጥናል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ መንግሥት የሚገቡ የውጭ ባንኮችን በማበረታታት በሀገር ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ያተረፉትን ትርፍ ወደ ውጭ የማውጣት ዕድል ከፍተኛ እንደሚሆን ስጋታቸውን አጋርተውናል፡፡ የሀገር ውስጥ ባንኮች ዕድሉን በአግባቡ በመጠቀም ተወዳዳሪና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሊሠሩ ይገባል፡፡

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 11 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You