የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ

አዲስ አበባ፦ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ እድሳት ተደርጎለት ከትናንት ጀምሮ ለአገልግሎትና ለጎብኚዎች ክፍት እንደሆነ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ገለጹ።

የካቴድራሉ አስተዳደሪ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ሲራክ አድማሱ እንደገለፁት፤ ካቴድራሉ እድሳት ሳይደረግለት ረጅም ጊዜ በመቆየቱ በውስጣዊና በውጫዊ የሕንፃው አካሉ ላይ የከፋ ጉዳት ደርሶበት ነበር።

ሕንፃው ከተጋረጠበት ጉዳት ለመታደግ ዕድሳት ማድረግ እንዳስፈለገ ያመለከቱት አስተዳዳሪው፤ ባለፉት 17 ወራት በምን መልኩ መታደስ እንደሚገባው ጥናት በማድረግ ወደ ሥራ ተገብቶ የዕድሳት ሥራውን በአሁኑ ጊዜ 95 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል። ከትናንት ጀምሮ ለአገልግሎትና ለጎብኚዎች ክፍት መሆኑንም ጠቁመዋል።

እስካሁን የተካሄደው የዕድሳት ሥራ 773 ቀናት እንደወሰደ ጠቁመው፤ ዕድሳቱን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 225 ቀናት እንደሚያስፈልጉ አባ ሲራክ አስረድተዋል። ለዕድሳት ሥራው 172 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር እንደሚፈጅ ገልጸው፤ እስከአሁን ለሥራ ተቋራጩ 124 ሚሊዮን 800 ሺህ ብር ክፍያ መፈጸሙን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ለሥራ ተቋራጩ ያልተከፈለ 47 ሚሊዮን ብር ቀሪ ሂሳብ ስላለ ይህንን ክፍያ አጠናቆ ለመክፈል ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም በመላው ዓለም በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች በቀጥታ ስርጭት የገንዘብ መሰብሰብ ፕሮግራም እንደሚካሄድ ተገልጿል። በቀጥታ የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራሙ የቤተክርስቲያንቱ ምዕመናን ብሎም መላው ኢትዮጵያውያን የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

ካቴድራሉ በቤተ ክህነት ደረጃ በከፍተኛ የመሪነት ቦታ ላይ ሆነው ይመሩ የነበሩ እንዲሁም የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጠብቀው በነፃነት የምንኖርባት ነፃ ሀገር ያስረከቡን ጀግኖች አርበኞች፣ የጦር መኮንኖች መካነ እረፍት ሥፍራም እንደሆነ አመልክተዋል። ይህን ታሪካዊ ሥፍራ አድሶ እና አስጠብቆ ወደ ቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ከአክሱም ፅዮን ቀጥሎ ትልቅ መንፈሳዊ ሥፍራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ካቴድራሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብሎም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርስ መሆኑን ተናግረዋል። ካቴድራሉን የማደስ ሥራ የሚከናወነው በቫርኒሮ ኮንስትራክሽን እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You