አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ እና የቀጠሉ ችግሮችን ለማከም የሚያስችል የሽግግር ፍትሕን ለማስፈን መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነ ብርሃን (ዶክተር) አስታወቁ። የፍትሕ ዘርፉን ዘመናዊ፤ ቀልጣፋ እና የሕዝብ አመኔታን ያተረፈ እንዲሆን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመለከቱ።
ሚኒስቴር ዴኤታው ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ በሀገሪቱ በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ፣ የቀጠሉ፣ ተደራራቢ እና ሰፊ የተጎጂና የአጥፊ ወሰን ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ ያልጠሩ ትርክቶች እና በደሎችን ለመፍታት የሚያስችል የሽግግር ፍትሕ ለማስፈን የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በእውነት፣ በእርቅ፣ በምሕረት እና በፍትሕ ላይ የተዋቀረ እና በግልፅ የሚመራ ሁለንተናዊ የሽግግር ፍትሕ ስልትን በተደራጀ፣ በተቀናጀ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበር ያስችል ዘንድ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲፀድቅ መደረጉንም ገልጸዋል።
ፖሊሲውንም ለማስፈፀም የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የተናገሩት ኤርሚያስ የማነ ብርሃን (ዶ/ር)፤ በቀጣይም የሽግግር ፍትሕን ለማስፈፀም የሚያግዙ የባለድርሻ አካላት ሚናን የመለየት እና የሽግግር ፍትሕ ተቋማትን የማቋቋም ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
ከዚሁ ጎን ጎን የሽግግር ፍትሕ ለማቋቋም የሚያስችሉ ሕጎችን የዘርፉ ባለሙያዎችን በማስተባበር ማውጣት መቻሉን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የሽግግር ፍትሕ ልዩ ችሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ የዓለም አቀፍ ጉልህ ወንጀሎች ረቂቅ አዋጅ፣ የሽግግር ፍትሕ ልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ የእውነት አፈላላጊና የይቅርታ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅና የተቋምና የሕግ ሪፎርም ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጆች ዝግጅት መጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።
ከሽግግር ፍትሑ ባሻገርም እንደሃገር የፍትሕ ዘርፉን ዘመናዊ፤ ቀልጣፋ እና የሕዝብ አመኔታን ያተረፈ እንዲሆን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የተናገሩት ኤርሚያስ የማነ ብርሃን (ዶ/ር)፤ የማሻሻያ ሥርዓቱ የዳኝነት ዘርፉን ለማሻሻል እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳብራሩት፤ ውጤታማ፣ ቀልጣፋ፣ ግልፅ፣ ወጪ ቆጣቢና አካታች የሆነ የፍትሕ ሥርዓት ለመፍጠር ሕግ ማውጣትና ተቋም መፍጠር ብቻ ሳይሆን አሠራሩን ዘመናዊ ማድረግ ይጠበቃል። ከዚህ አንፃር የፖሊሲ ተቋማትን ፤ ፍርድ ቤቶችንና ፍትሕ ሚኒስቴርን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የማጠናከር ሥራዎች ተጀምረዋል።
በተለይም የዳኝነት ሥርዓቱ ነፃ እና ገለልተኛ እንዲሆን በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ያስረዱት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ በተለይም የዳኝነት አካሉ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የፀዳ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።
ከለውጡ በፊት ዳኞች የሚሾሙበት ሁኔታ በአብዛኛው በፖለቲካ ተፅዕኖ እንደነበር አውስተው፤ በሪፎርሙ የዳኞች ሹመት፣ ምልመላ፤ ዝውውር ሥርዓት ባለው መልኩ ለመምራት ይቻል ዘንድ በአዋጅ ደረጃ ፀድቆ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም