አየር መንገዱ ወደ እሥራኤል የሚያደርገው በረራ የሀገራቱን የጠበቀ ግንኙነት የሚያሳይ እንደሆነ ተገለጸ

እየሩሳሌም:- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁኔታዎች ሳይገደብ ወደ እሥራኤል የሚያደርገው በረራ የሁለቱን ሀገራት የጠበቀ ግንኙነት የሚያሳይ መሆኑን የእሥራኤል ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሸረን ሜሬየም ኸስኬል ገለጹ።

ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሸረን ሜሬየም ኸስኬል ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ በርካታ አየር መንገዶች ወደ እሥራኤል የሚያደርጉትን በረራ ባቋረጡበት ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እሥራኤል የሚያደርገውን በረራ ባለማቋረጡ አመስግነዋል።

አየር መንገድ በሁኔታዎች ሳይገደብ ወደ እሥራኤል የሚያደርገው በረራ የሀገራቱን የጠበቀ ግንኙነትና ለጋራ ጥቅም አብሮ መሥራትን ያሳየ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያና እሥራኤልን ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እና የሚጋሯቸው ሃይማኖታዊ እሴቶች አሏቸው ያሉት ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ይህም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የጠበቀ እንዲሆን ማስቻሉን ገልጸዋል።

በእሥራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዲቪዥን ቢሮ ኃላፊ ኖአ ፉርማን በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ወደ እሥራኤል የሚያደርገውን በረራ ለማስቀጠል ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በሚኒስቴሩ የደቡብ አፍሪካ ሪጅን ዳይሬክተር በላይነሽ ዘቫዲያ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና እሥራኤል እየተፈተነች ባለችበት ወቅት ያልተቋረጠ አገልግሎት መስጠቱን አስታውሰው፤ በአስቸጋሪ ጊዜያትም ወደ እሥራኤል የሚያደርገውን በረራ ቀጥሏል፤ ይህም ለጠንካራ ግንኙነታችን ማሳያ ነው” ብለዋል።

ዳይሬክተሯ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁለትዮሽ ግንኙነትን በማጎልበት ረገድ ያለውን ወሳኝ ሚና ጠቅሰው፣ “ኢትዮጵያ ለእሥራኤል እውነተኛ ወዳጅ ነች” ሲሉ ገልጸዋል። አየር መንገዱ በአገልግሎቱ ያሳየውን ቁርጠኝነት በመግለጽ፣ ይህም በእሥራኤል መንግሥትና ሕዝብ የተመሰገነ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ኢዩኤል ክፍሉ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You