የ19 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ የጋራ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ በሃገር አቀፍ ደረጃ የአየር ብክለት መጠንን ለመቀነስ፣ ፅዱና ከብክለት የፀዳች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያግዝ ከ19 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግበትን ፕሮጀክት ለመተግበር የጋራ ስምምነት ተፈርሟል።

ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነትም በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በከተማና መሠረተ ልማት፣ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ መካከል የመግባቢያ ስምምነት ትላንት ተፈርሟል።

በፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት ተግባራዊ በሚደረገው ፕሮጀክት ትግበራ የመግባቢያ ስምምነት ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደገለፁት፣ የአየር ብክለት በአካባቢ ብሎም በሰው ልጆች ጤና በተለይ በሕፃናት በእናቶች ላይ ከባድ ጉዳትና ህልፈትን የሚያስከትል ነው። በኢትዮጵያም በየዓመቱ ከ 39 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ህልፈትና ለበርካቶች የአስም፣ የሳንባ፣ የልብ፣ የኩላሊትና የጉበት ሕመም መንስኤ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል።

መሰል ቀውስን የሚያስከትለውን አየር ብክለት ጨምሮ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥት ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ስለመሆኑ ያስገነዘቡት ዶክተር ደረጄ፣ ሕጎችን በአግባቡ ማስተግበር፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ማስፋት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ማብዛት፣ ፅዱና ከብክለት የፀዳች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የኮሪደር ልማትን የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም የዚሁ አካል መሆናቸውን አብራርተዋል።

እነዚህና መሰል እርምጃዎችም ከተማን ከማዘመን ባሻገር የአየር ብክለትን በመቀነስ ረገድ አይነተኛ አስተዋፅዖ እያደረጉ መሆናቸውን ያስገነዘቡት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከ19 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግበት በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረው ፕሮጀክትም፣ በሃገር አቀፍ ደረጃ የአየር ብክለት መጠን ለመቀነስ፣ ፅዱና ከብክለት የፀዳች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ነው›› ብለዋል።

በትግበራው በተለይ በጤናው ዘርፍ በተቋማት ውስጥ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ማዘመንና የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችን በአግባቡ ማስወገድን ጨምሮ የተለያዩ ለብክለት መንስኤዎችን የማስተካከልና የመቆጣጠር ተግባራት እንደሚከናወኑም አስረድተዋል። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሦስት የአየር ብክለት መለኪያ መሣሪያዎች አቅም ማጎልበትና የማስፋት ሥራ እንደሚከናውንም ጠቁመዋል።

የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው፣ ‹‹ፕሮጀክቱ በቀጣይ አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆንና የአየር ጥራትን ማረጋገጥ፣ በብክለት ምክንያት በሰው ልጆች ላይ የሚደርስ ሞት መቀነስና በአካባቢ ላይ የሚደርስ ጉዳትን ማስቀረትን ዓላማው ያደረገ ነው›› ብለዋል።

በስምምነቱ በተቋማት የሚተገብሩ ሥራዎች በዝርዝር መለየታቸውና ፅዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት ሁሉም የቤት ሥራውን በትኩረት መሥራት እንዳለበት ያመላከቱት ኢንጂነር ለሊሴ፣ በየወሩም በአካባቢ ጥበቃና በጤና ሚኒስቴር በሚመራ ኮሚቴ አፈፃፀሙ በትኩረት የሚገመገም መሆኑን አስገንዝበዋል።

ስምምነቱን የፈረሙት ተቋማት አመራሮችም፣ በቀጣይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተቀናጀ መልኩ የአየር ብክለት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You