በክልሎቹ የወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመግታት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፦ በክልሎቹ የወባ በሽታ ወረርሽኝን ለመግታት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያና የሲዳማ ክልሎች ጤና ቢሮዎች ገለጹ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ባለፉት አራት ወራት በክልሉ ከፍ ያለ የወባ ወረርሽኝ ስርጭት ተከስቶ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ በተሠራው ሥራ ስርጭቱ እንዲቀንስ ተደርጓል።

የወባ ወረርሽኙ በተለየ ሁኔታ የተስፋፋባቸውን አካባቢዎች በመለየት እነዚህ አካባቢዎችን መሠረት ያደረገ ሥራ በመሥራትና የክልሉን አመራር በማሳተፍ በሽታውን ለመቆጣጠር ጥረት እንደተደረገ ተናግረዋል።

በሽታውን ለመከላከል የሚያግዙ እንደ አጎበር ያሉ ቁሳቁሶችን በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ በኅብረተሰቡ ዘንድ የነበረው የግንዛቤ እጥረት ወረርሽኙን በቀላሉ መቆጣጠር እንዳይቻል ምክንያት ሆኗል ያሉት አቶ ማሙሽ፤ ይህንን ችግር ለመፍታትም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር በትኩረት ተሠርቶ በአጭር ጊዜ ውጤት እንደተገኘ አብራርተዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 80 በመቶ የሚሆኑ ወረዳዎች ለወባ በሽታ ተጋላጭ ናቸው ያሉት አቶ ማሙሽ፤ በክልሉ ከ600 ሺህ በላይ ቤቶች ላይ ቤት ለቤት አሰሳ ማድረግ ተችሏል፤ በዚህም የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች ሕክምና እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

በሽታውን በዘላቂነት ለመከላከልም አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚሆን አጎበር ማሰራጨት ተችሏል፤ በተጨማሪም በሽታው በስፋት በሚታይባቸው 31 ወረዳዎች ላይ የኬሚካል ርጭት ተደርጓል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሚሆኑ እናቶችና ሕፃናትን ሕይወት ለመታደግ ርብርብ መደረጉን አንስተዋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በላይነህ በቀለ በበኩላቸው፤ በክልሉ የወባ በሽታ ለመከላከል በተሠራው ሥራ የበሽታውን መስፋፋት መግታት ተችሏል።

በቀሩት ሦስት አካባቢዎች አሁንም የበሽታው ምልክት በስፋት ይታያል። ይህንን መነሻ በማድረግ አመራሩን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ሥራ በመሥራት ወረርሽኙ በኅብረተሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

አካባቢን ፅዱ ማድረግና የአልጋ አጎበር በአግባቡ መጠቀም የወባ በሽታ ለመከላከል አስተዋፅዖው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ኅብረተሰቡ እነዚህን የመከላከያ መንገዶች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲያደርግ የግንዛቤ መፍጠር ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

እስከአሁን በክልሉ አንድ ሰው በወባ በሽታ ምክንያት ሕይወቱን ማጣቱን የተናገሩት አቶ በላይነህ፤ በቀበሌ ደረጃ ያሉ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በሠሩት ጠንካራ የመከላከል ሥራ የሰዎችን ሕይወት መታደግ መቻሉን አንስተዋል።

በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከል ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ 915 ሺህ የአልጋ አጎበር ተሰራጭቷል፣ በተጨማሪም በአራት ወረዳዎች በሚገኙ 23 ቀበሌዎች የኬሚካል ርጭት ተካሂዷል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የኬሚካል ርጭቱ ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ በሚታይባቸው አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በክልሎቹ በበሽታው የተያዘ ሰው ሕክምና ለማግኘት ወደ ጤና ተቋማት ሲሄድ በቂ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችል የጤና ተቋማትን በግብዓት የማሟላት ሥራ እንደተሠራ አብራርተዋል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You