የተማሪዎች ሥነ ምግባር ጉዳይ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ያወጣው መመሪያ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ሲጋራ ሲያጨስ የተገኘ ተማሪ ከትምህርት ቤት ለአንድ ዓመት እንደሚያግድ የሚናገሩት በአንዶዴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ወ/አብ እሸቱ፤ እሳቸው በሚሠሩበት ትምህርት ቤት ድርጊቱን ሲፈፅሙ የተያዙ ተማሪዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

ነገር ግን ቤተሰብ በመጥራት ተመካክረንና ለተማሪዎቹም ምክር ሰጥተን ድጋሚ በዚህ ድርጊት ከተገኙ እርምጃው እንደሚወሰድባቸው በማስጠንቀቅ በይቅርታ ያለፍንበት ሁኔታ አለ ይላሉ።

ትምህርት ቤት ማረቂያ፣ ማረሚያና ማስተካከያ ነው የሚሉት ምክትል ርዕሰ መምህሩ፤ በሕጉ መሠረት ከዚህ ብናስወጣቸው ሊገጥማቸው የሚችለውን ከዚህ የከፋ ነገር በማሰብ ይቅርታው እንደአማራጭ መወሰዱን ይገልፃሉ።

ለሌሎች የሥነምግባር ችግሮችም ወደ እርምጃ ከመግባታቸው በፊት የሚወስዷቸው እርምቶች መኖራቸውን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መምህሩ፤ ካልሆነ ግን እርምጃዎቹን ለመውሰድ እንደሚገደዱ ያስረዳሉ።

ምክትል ርዕሰ መምህሩ እንደሚሉት ትምህርት ቤቱ በተማሪዎች ሥነምግባር ዙሪያ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ የተማሪ ክበባትን ማደራጀት አንዱ ነው። ትምህርት ቤቱ በሥነ ምግባር ላይ የሚሠሩ የተለያዩ የተማሪ ክበባት አሉት። እንደ ምሳሌም በተማሪዎች ሚኒ ሚዲያ ክበብ አማካኝነት በተለያዩ ቋንቋዎች የተማሪዎችን ሥነ ምግባር በተመለከተ መልዕክቶች ይተላለፋሉ ነው ያሉት።

ከሚኒ ሚዲያ ክበብ በተጨማሪም የፀረ ሙስና ክበብና የተማሪ ትራፊክ ክበብ እንዳለ ገልፀው፤ የተማሪዎች ፓርላማንም አደራጅተውና ሚኒስትሮችን አስመርጠው በጉዳዩ ዙሪያ እየሠሩ መሆኑን ይገልፃሉ። እነዚህ ሥራዎችም የመማር ማስተማር ሂደቱን ሠላማዊ እንዳደረጉት ያስረዳሉ።

በተለይም ከባለፈው ዓመት ወዲህ በሥነ ምግባር ዙሪያ የተለያዩ ለውጦች እንዳሉ ገልፀው፡- አሁን ላይ ጉዳዩ አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ አለመሆኑን ይጠቁማሉ። በፊት በፊት ይታዩ የነበሩ የቡድን ፀቦች እንደነበሩ አስታውሰው፡- አሁን ላይ ካለው ክትትልና ቁጥጥር አኳያ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ችግሩ መቀረፉን ይገልፃሉ።

አርፋጅ ተማሪዎችን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ያረፈደ ተማሪ በዩኒት ሊደር፣ ሁለተኛ ሲያረፍድ ዩኒት ሊደርና የክፍል ኃላፊው፣ ሦስተኛ ሲያረፍድ ደግሞ ወላጁንና ራሱን ተማሪውን በማድረግ የሚመከርበት ሁኔታ ስላለ እንደ ማርፈድ ያሉ ችግሮች እየቀነሰ የሄደበት አግባብ እንዳለ ያብራራሉ።

በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ በላይ ወልደፃዲቅ፤ በበኩላቸው በፊት ከነበረው አኳያ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ማርፈድ እየቀነሱ፣ የሰልፍ ሥነ ሥርዓት ላይ እየተገኙና የሕዝብ መዝሙር እየዘመሩ መሆናቸውን ይገልፃሉ።

የሥነምግባር ችግር ባለባቸው ተማሪዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተም በመጀመሪያ እርስ በእርሳቸው ማለትም በተማሪዎች እንዲመከሩ እንደሚደረግ ገልፀው፤ በዚህ ምክር በቀላሉ የሚመለሱ እንዳሉ ያስረዳሉ። የተወሰኑት ደግሞ በመምህራን ተመክረው የሚመለሱ እንዳሉም ይጠቅሳሉ። ከዚህ ካለፈ ደግሞ በምክትል ርዕሰ መምህር ይመከሩና አልፈው ከመጡ ርዕሰ መምህር ወላጅ ጠርቶ ቃለጉባኤ በመያዝ የተማሪውን ሥነምግባር ከመመለስ አኳያ የሚሄዱበት አግባብ እንዳለ ያብራራሉ።

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተማሪ ተወካዮች፣ ወላጆች፣ መምህራንና የፀጥታ አካላት ጋርም በጋራ እየሠሩ እንዳሉ ይገልፃሉ። ከዚህ ባሻገርም በትምህርት ቤቱ የሞባይል ስልክ ይዞ መገኘት እንደማይቻል ገልፀው፤ ይህ እንዳይሆን ተፈትሸው እንደሚገቡ ያስረዳሉ። በዚህ ዓመት ሱስ ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ተለይተው የተያዙ ወደ ሰባት የሚጠጉ ተማሪዎች እንዳሉ ገልፀው፤ ከትምህርት ቤት ማገዱ መፍትሔ ስለማይሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚለወጡበት መንገድ ላይ እየሠሩ እንዳሉ ያስረዳሉ። እነርሱን የመለየቱ ሥራም ሱስ ያለባቸው ተማሪዎች ምን አይነት ባሕሪ ያሳያሉ ከሚለው በመነሳትና ሥልጠና በመስጠት በተማሪ ተወካዮች አማካኝነት እንደተሠራ ያስረዳሉ።

ከመለየቱ ባሻገርም ሥልጠና በመስጠትና ሰው መድቦ ክትትል በማድረግ ከሰባቱ ተማሪዎች ሦስቱ ከሱሱ የወጡበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቁማሉ።

የትምህርት ሥራ የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል የሚሉት ርዕሰ መምህሩ፤ ሁሉም ተቀናጅቶ የተማሪዎችን ሥነምግባር በማረቁ ረገድ ቢሠራ ተማሪዎች ላይ የተሻለ የባሕሪ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ተማሪዎች በትምህርት ቤት በጥሩ ሥነ-ምግባር በመታነጽ ለራሳቸውም ሆነ ለማኅበረሰባቸው እንዲሁም ለሀገራቸው ጠቃሚ ዜጋ ሆነው ሊቀረጹ እንደሚገባ በማመን የተማሪዎች የሥነ-ምግባር ችግር በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ እየፈጠረ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማስተካከል ያለመ የተማሪዎች የሥነ ምግባር መመሪያ ቀርፆ እየሠራ እንደሚገኝ ይታወቃል። የሥነምግባር ጉዳይ ትውልድን ከማነፅ አኳያ ያለው ሚና አይነተኛ ነውና በዚህ ረገድ በከተማዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች አሁን ላይ ምን እየሠሩ ይገኛል?

ነፃነት ዓለሙ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You