‹‹በምትክ ቤቱ ላይ ቅሬታ አቅርበን ጠብቁ በተባልንበት የቤታችን መብራት ተቆርጦብናል´ – እነ ወይዘሮ እየሩሳሌም ታዬ

‹‹ሰው ቤት ውስጥ እያለ እኛ የቆረጥነው መብራት የለም´ – በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

አዲስ አበባ፡- የልማት ተነሽ በመሆናችን በምትክ ቤቱ ላይ ቅሬታ አቅርበን ጠብቁ በተባልንበት የቤታችንን መብራት ተቆርጦብናል ሲሉ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ ነዋሪዎች እነ ወይዘሮ እየሩሳሌም ታዬ ቅሬታቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገለጹ።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደምሰው ትኩ በበኩላቸው ሰው ቤት ውስጥ ሰው እያለ እኛ የቆረጥነው መብራት የለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ እየሩሳሌም ታዬ ለኢፕድ እንደተናገሩት በኮሪደር ልማቱ ተነሺ ሲሆኑ የሚፈርሰው ለልማት በመሆኑ ምንም አይነት ቅሬታ እንደሌላቸው ይናገራሉ። ነገር ግን አብረዋቸው ከሚኖሯቸው የቤተሰብ አባላት ውስጥ ዓመት ያልሞላት “የዳውንሲንደረም” ሕመም ተጠቂ፤ የልብ ሕመምተኛ የሆነች የእህታቸው ልጅ እና የሚያሳድጓት የአዕምሮ ሕመምተኛ ቤተሰብ አሏቸው።

ለልማት እንዲነሱ የቤት ዕጣ ሲያወጡ ዕጣቸው የደረሳቸው በበሻሌ አካባቢ መሆኑ የአዕምሮ ሕመምተኛ ለሆነችው ቤተሰባቸው፤ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምና ለምትከታተለው የ‹‹ዳውን ሲንድረም›› ተጠቂ እና የልብ ሕመምተኛ ለሆነችው የእህታቸው ልጅ ቦታው ሩቅ በመሆኑ ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ቅሬታ አስገብተው ቅሬታው ተቀባይነት ማግኘቱን ይናገራሉ። በተቋሙ ቅሬታውም ተቀባይነት በማግኘቱ ቤቱ እስኪቀየርላቸው ድረስም በልማት በሚፈርሰው ቤት ውስጥ እንዲኖሩ ተወስኖላቸዋል።

ታኅሣሥ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ግን በወረዳው ሠራተኛ የሆኑ ግለሰቦች የቅሬታ ሂደት ላይ እንደሆኑ እየታወቀ የቤታቸውን መብራት መስመር አቋርጠውት እንደሄዱ እና ጨለማ ውስጥ ሕመምተኛ ቤተሰብ ይዞ መቀመጥ ከባድ ስለሆነ ከፍተኛ መረበሽ ውስጥ እንዳሉ ገልጸዋል። ቆጣሪው ይነሳልን ጥያቄ ባላቀረብንበት ሁኔታ በቤቱ ውስጥ እየኖርን መብራት መቆረጡ ተገቢ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በወረዳው ቤቶች አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት አቶ ዐቢይ የሚባሉ ግለሰብ መስመሩ ሲቆረጥ በቦታው እንደነበሩ እና በስልክም ሲያነጋግሯቸው መስመሩን እንደሄደ እና ቦታውን መልቀቅ እንዳለባቸው እንደነገሯቸው ገልጸዋል። ወይዘሮዋም መነሳት ፍላጎት ቢኖራቸውም ቤቱን ስላልተረከቡ ፈራሽ የሆነውን ቤታቸውን ሊለቁ እንዳልቻሉ ነግረዋቸው የስልኩ ንግግር እንደተቋረጠ ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው ያሉ እና በልማት ተነሺ  የሆኑ ጎረቤቶቻቸው የመብራት መስመራቸው እንዳልተቋረጠባቸው ተናግረው፤ የእሳቸው መስመር ብቻ ተለይቶ መቋረጡ ምክንያቱ በወረዳው የሚሠሩ ባለሙያዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።

በልማቱ ደስተኞች መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮዋ ቤቱ እንደተሰጣቸውም ለመልቀቅ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው፤ ነገር ግን አሁን ይህ ባልሆነበት ሁኔታ መብራታቸውን መቋረጡ ተገቢ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። በቤቶች ልማት እና አስተዳደር በኩል ያለው ቅሬታን የመስማትና የመፍታት አካሄድ መልካም እንደሆነ አመልክተዋል።

ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ ወይዘሮ ሙሉነሽ ታደሰ እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም አቅመ ደካማ በመሆናቸው እና እግራቸውን በመታመማቸው በዕጣ የደረሳቸው ቤት እንዲቀየር ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አቤት ብለው ለቅሬታቸው ምላሽ ያገኙት 7/04/2017 ከሰዓት በኋላ ነው። ነገር ግን በወረዳው በኩል በ9/04/2017 እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ቤቱን ለቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው እና ቅሬታ ላይ የቆዩ ስለነበሩ ቤቱን ለመልቀቅ ዝግጅት አለማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የደረሳቸውን ቤት ለማስተካከል ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ቢናገሩም በዕለቱ ቤቱን ካለቀቁ የእቃ ማጓጓዣ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደማያገኙ እንደተነገራቸው አብራርተዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደምሰው ትኩ የልማት ተነሽዎች ወደ ደረሳቸው ቤት ሲገቡ መጨረሻ ላይ ቆጣሪ ይነሳልኝ ጥያቄ አቅርበው ይነሳል እንጂ በምንም ተዓምር ሰው ቤት ውስጥ እያለ እኛ የቆረጥነው መብራት የለም። ቅሬታውን እስካሁን አላውቅም፤ እንዲህ አይነት አሠራር የለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገለጻ፤ የኮሪደር ልማቱ ሥራ በአደረጃጀት የሚመራ ነው። መብራት የሚቆረጠው እያንዳንዱ ሰው ከቤቱ ወጥቶ ወደ ምትክ ወደተዘጋጀለት ቤት ከሄደ በኋላ ነው። ይህ ሲሆንም ነዋሪዎች ቆጣሪ ይነሳኝ ብለው ሲያቀርቡ የመብራት ኃይል ሠራተኞች ጠርተን የሚቆረጥበት አሠራር ነው ያለው።

ትናንት ተቆረጠብን ስለተባለው የመብራት ቅሬታ

መብራት እንዲቆረጥ ተብሎ የተጠራ የመብራት ኃይል ሠራተኛ የለም። ቅሬታ ያቀረቡ ነዋሪዎች ካሉ የተነሱትን ሲቆርጡ በስህተት ከቆረጡባቸው ችግሩን እንቀርፋለን።

በተቀናጀና በተናበበ መንገድ በቁጥጥርና በክትትል የምትሠሩ ከሆነ ከአንድ የመብራት ፖል ላይ መብራት ሲቆረጥ እኛ አናውቅም ማለት መናበቡን ጥያቄ ውስጥ አያስገባም ወይ ተብሎ ለተነሳቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ በዕለቱ የተጠራ የመብራት ኃይል ሠራተኛ የለም። ቅሬታው በምን ሁኔታ እንደቀረበ አላውቅም። ነገር ግን ማንም ይቁረጥ ማን ችግሩን እንፈታለን ነው ያሉት።

ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አቤት ብለው ለቅሬታቸው ምላሽ ያገኙት በ7/4/2017 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ነው። ነገር ግን በወረዳው በኩል በ9/4/2017 ዓ.ም እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ቤቱን ለቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው ገልጸዋል። በዚህ ሀሳብ ላይ ምላሽዎት ምንድን ነው? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ደምሰው በምላሻቸው ቤታቸውን አይተው ለመግባት ከተዘጋጁ በኋላ እንጂ ዛሬውኑ ተነሱ የሚል አካል የለም ብለዋል።

ይህ ከሆነ የቅሬታው ምንጩ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ? የሚነሱት እያንዳንዱ ነገር ከተዘጋጀላቸው እና የሚስፈልጋቸውን መሠረተ ልማት ከተሟላ በኋላ እንጂ እንዲሁ የሚነሱበት አሠራርም አግባብ የለም። ቅሬታ ያላቸው ሰዎች ቅሬታው እስኪፈታላቸው እንጠብቃለን።

ቅሬታቸው ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ቤታቸው ለመግባት የዝግጅት ጊዜ ተነፍጎኛል ጥድፊያ ሆኖብኛል የሚል ቅሬታ አንስተዋልና ምላሽዎት ምንድን ነው? በምንም ተዓምር እቃ የሚጭኑት በተዘጋጁ ሰዓት እና ጫኑልን ባሉን ጊዜ ነው እንጂ በግዴታ የሚሠራ ሥራ የለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ወረዳ ላይ ያሉ አንዳንድ ባለሙያዎች ለተነሽዎች የመልካም አስተዳደር ቅሬታ ምንጭ እንደሆኑ ይነገራል። እዚህ ላይ አስተያየትዎት ምንድነው? የባለሙያዎች ቁጥጥር እና ክትትሉ እስከ ምን ድረስ ነው? ሠራተኞች በትክክል እንቆጣጠራለን። በቁጥጥሩ ግን የዲስፕሊን እርምጃ የተወሰደበት ሠራተኛ የለም። እስካሁን ስድስት የሚደርሱ ቅሬታዎች ቀርበውልን አምስቱን በተገቢው መንገድ ምላሽ ሰጥተናል ሲሉ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ተናግረዋል።

በሞገስ ተስፋና መክሊት ወንደወሰን

አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You