– በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞችና አካባቢዎች ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሄደ
አዲስ አበባ:– በክልላችን የተካሄደው ሠላማዊ ሰልፍ ሕዝባችን ምን ያክል ሠላም እንደሚሻ ያሳያበት ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መንግሥት የሚያከናውነውን የሠላም ማስከበር ተግባርና የልማት ሥራዎችን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ “ሠላም ለሁሉም ሁሉም ለሠላም” በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በአማራ ክልል የተካሄደውን ሠላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ሠላማዊ ሰልፉ ግጭት በቃን፣ የምንፈልገው ሠላምና ልማት ነው የሚል መልዕክት የያዘ ነው። ሠላማዊ ሰልፉ ሕዝባችን ምን ያክል ሠላም እንደሚሻ ያሳየበት ነው ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ሰልፎች እንዳይካሄዱ ለማስፈራራት እና ለማሸበር የተደረገው ጥረትም አልተሳካም ነው ያሉት። ሕዝቡ ግን ዛቻ እና ማስፈራሪያዎችን በመተው ሠላምን እንደሚፈልግ በነቂስ ወጥቶ አሳይቷል ብለዋል።
ሰልፉ ጥያቄ አለኝ የሚል ኃይል ሁሉ ችግሮችን በውይይት ነው መፍታት የሚገባው የሚለውን የሚያሳስብ መሆኑንም አመላክተዋል። ሕዝብ ከጎናችን ነው እያለ መንግሥትን በኃይል እናስወግዳለን የሚለውን ኃይል ያጋለጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ሰልፉ እንደ መንግሥት ልዩ ትርጉም አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መንግሥት ለሠላም ያደረገውን ጥረት በአደባባይ ወጥቶ የደገፈበት ነው ብለዋል።
በሰልፉ ሕዝቡ መንግሥትን ብቻ አይደለም የደገፈው፣ የደገፈው ሠላምን ነው ብለዋል። ሠላም ሲሆን ለመንግሥት ትልቅ አቅም መሆኑን ነው የተናገሩት።
የተደረገው የሠላም ሰልፍ በቀጣይ ለሚደረገው ሠላማዊ እንቅስቃሴ ጉልበት የሚፈጥር ነው ብለዋል። በሕዝባችን ትልቅ ኩራት ተስምቶኛል፣ ምስጋናም እናቀርባለን ነው ያሉት። ሕዝቡ በሠላም ወጥቶ እንዲገባ ላደረጉ የፀጥታ ኃይሎች ምስጋና አቅርበዋል።
ሰልፉ ወደፊት ለሚደረገው የሕግ ማስከበር እና የሠላም ሥራ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ነው ያሉት። መንግሥት ሠላማዊ አማራጮችን ቀዳሚ የችግር መፍቻ አድርጎ እንደሚጠቀምም አስታውቀዋል። አውዳሚ ተግባርን አንመርጥም፣ የምንመርጠው ዘላቂ ሠላምን የሚያመጣውን ሠላማዊ አማራጮችን ነው ብለዋል።
እንደ አሚኮ ዘገባ ችግሩ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሠላም አማራጮችን መፈለጋቸውን እና ማስቀመጣቸውን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሠላም አማራጭ ለይስሙላ የምናደርገው ሳይሆን አምነንበት እና አዋጭ መሆኑን ተረድተን የምናደርገው ነው ብለዋል።
የክልሉ ሕዝብ በአንድነት ወጥቶ ባሳየው የሠላም ፍላጎት ኮርተናል፣ ምስጋናም ይገባዋል ብለዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ትናንት በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች፣ የገጠር ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ሕዝባችን ‘’ሠላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሠላም’’ በሚል መሪ ሀሳብ በነቂስ ወጥቶ ላሳየው የሠላም የድጋፍ ሰልፍ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
ሠላም ወዳዱ ሕዝባችን መንግሥት ለሠላም እያቀረበ ያለውን ተደጋጋሚ ጥሪ በመደገፍና ፅንፈኝነትን በማውገዝ የታጠቁ ቡድኖች ወደ ሠላም እንዲመጡ ጥሪ አቅርቧል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአማራ ክልልን የሠላምና የልማት ማዕከል ለማድረግ ሁሉም ለሠላም ዘብ ሊቆም ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
መንግሥት ሁልጊዜም ቢሆን ለሠላም በሩ ክፍት በመሆኑ ትጥቅ ያነሱ ቡድኖች ፅንፈኝነት እና ግጭት ማንንም እንደማይጠቅም በመገንዘብ ወደ ሠላማዊ መድረኩ እንዲመጡ ጥሪ እናቀርባለን ነው ያሉት።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክትም፤ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሕዝቡ በነቂስ በመውጣት በክልሉ ሠላም እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ በንፁሓን ላይ ግፍ እየፈፀሙ የሚገኙ ፅንፈኛ ኃይሎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ መንግሥት በተደጋጋሚ እያቀረበ ለሚገኘው የሠላም ጥሪ ድጋፍ እንደሚቸር በይፋ ድምፁን ማሰማቱን ገልጸዋል።
የክልሉን ሕዝብ ላቀረበው የሠላም ጥሪም ምስጋናቸውን አቅርበው፤ በቀጣይም ክልሉ በተሟላ ሁኔታ ዳግም ወደ ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
“በመንግሥት በኩል ለሠላም፣ ለውይይትና ድርድር የምትጠልቅ ጀምበር እንደሌለችም ደጋግመን ማረጋገጥ እንወዳለን” ሲሉ አቶ አደም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
ስለሆነም በአማራ ክልል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት በኃይል አማራጭ የሚገኝ መፍትሔ አለመኖሩን በመረዳት በዛሬው ሰልፍ ጨምሮ ሕዝቡ በተደጋጋሚ እያነሳቸው ያሉ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ፣ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች እየታየ እንደሚገኘው በአስቸኳይ ወደ ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በደሴ፣ በደብረማርቆስ፣ በሰቆጣ፣ እንጅባራ፣ደብረ ብርሃን፣ በአርጎባ በደባርቅ፣ በደብረታቦር፣ በኮምቦልቻ፣ በሌሎች ከተሞችና የገጠር ወረዳዎች ትናንት ሕዝባዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።
በሰልፉ የተሳተፉ እንዳሉት፤ ክልላችን ጦርነት ሳይሆን ሠላምና ልማት ነው የሚያስፈልገው፣ መንግሥት ሕግ በማስከበር የዜጎችን ሕይወት መታደግ አለበት የሚሉና ሌሎችን መልዕክቶች አስተላልፈዋል።
ፅንፈኛው ኃይል በንጹሓን ላይ የሚፈጽመው ግድያና መፈናቀል ሊቆም ይገባል፣ የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌዴራልና የክልላችን የፀጥታ ኃይሎች ለከፈሉት ዋጋ ክብር እንሰጣለን ብለዋል። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፅንፈኞችን በማውገዝ የሕግ ማስከበሩን ተግባር የሚደግፉ መልዕክቶችንም አስተላልፈዋል።
ክልላችንን የሠላምና የልማት ማዕከል ለማድረግ ሁላችንም ለሠላም ዘብ እንቆማለን፤ በግጭት የሚፈታ ምንም ነገር እንደሌለ ሁሉም ተገንዝቦ ታጣቂ ኃይሎች ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት መነጋገርና መወያየት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
“በንፁሓን ላይ የሚፈፅመው ግድያ፣ ማገትና ማፈናቀል ሊቆም ይገባል፤ ንጹሓን በመጨፍጨፍ አማራን ነፃ ማውጣት አይቻልም፤ መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያደርገውን የሠላም ጥሪ እንደግፋለን፤ የልማት ማዕከል የነበረውን ክልላችንን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ የሚሠራው ሥራ የባንዳነትና የፅንፈኝነት ጥግ ነው” የሚሉ እና ሌሎች ዘላቂ ሠላምና ልማትን የሚጠይቁ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
እንዲሁም ሰልፈኞቹ “ሠላም ተጠምተናል”፣ “ሠላም የጋራ ሐብት ነው”፣ “ከሠላም ዕጦት ያጣነው እንጂ ያተረፍነው የለም”፣ “መንግሥት በተደጋጋሚ ያደረገውን የሠላም ጥሪ እንደግፋለን”፣ “ንፁሐንን በግፍ መጨፍጨፍ አረመኔነት በመሆኑ እናወግዛለን” የሚሉና መሠል መፈክሮች በሰልፎቹ ተሰምተዋል።
የክልሉ ፖሊስ ባወጣው መግለጫም÷ የአማራ ክልል ሕዝብ ለዓመታት የተደቀነበትን የሰቆቃ ቀንበር የሚያወግዝ ሠላማዊ ሰልፍ “ሠላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሠላም” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ከተሞች ማካሄዱን አንስቷል።
ለዓመታት ክልሉ በራሱ አለሁ ባይ ፅንፈኛ ኃይሎች ምክንያት በሰቆቃ ሕይወት ውስጥ እንዲጓዝ፣ እንዲዘረፍ፣ እንዲፈናቀልና እንዲሰደድ መደረጉን ጠቁሞ፤ ይህን የመከራ ቀንበር የተሸከመው የክልሉ ሕዝብ የሠላም ካውንስል እስከመወከል የደረሰ “ሠላሜን መልሱልኝ” ጥያቄውን ከጀመረ መሰነባበቱን ጠቅሷል።
ይሁን እንጂ ፅንፈኛው ኃይል የማኅበረሰብን የሠላም ጥያቄ “ጆሮ ዳባ ልበስ…” በማለት ከሰብል ማቃጠል ጀምሮ የክልሉን ሕዝብ ባሕልና ወግ የማይገልጽ፣ ዘመኑን የማይመጥንና ፀያፍ ተግባር መፈጸሙንም አስታውሷል። በትናንትናው ዕለትም የፅንፈኛውን ተግባራት የሚያወግዝ ሰልፍ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ተካሂደው በስኬት መጠናቀቃቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም