አዲስ አበባ፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶች ላይ በተፈጸመ ስርቆት የአንድ ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንዳጋጠመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ። ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ለግብዓትነት የሚጠቀሙትን ብረት ሕጋዊነት በማረጋገጥ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በ2015/16 ዓ.ም ብቻ ተቋሙ በሚያስተዳድራቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶች ላይ በተፈጸመ ስርቆት የአንድ ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ኪሳራ አጋጥሟል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሀገር አቀፍ ደረጃ የኃይል ማመንጫ፣ ማከፋፈያ እና የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቶችን ይገነባል፤ ያስተዳድራል ያሉት ኃላፊው፣ ለፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሶ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ይህም ሆኖ መሠረተ-ልማቱ ላይ በሚደርስ ስርቆት ኪሳራ እያጋጠመው መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይም በከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈጸመው ስርቆት የከፋ እንደሆነና ምሰሶዎችን ሙሉ ለሙሉ እስከመጣል የሚደርስ፤ የኤሌክትሪክ ፍሰትን እስከ ቀናት ብሎም እስከ ወራት በሚዘልቅ ሁኔታ የሚያስተጓጉል እንደሆነ አስታውቀዋል። ተቋሙ የሚሰረቁ ብረቶችን ለመተካት ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጣና በሚቋረጠው የኤሌክትሪክ ፍሰት ምክንያትም ማግኘት የሚገባውን ከፍተኛ ገቢ እያጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
በ2015 ዓ.ም ተቋሙ በስርቆት ምክንያት 700 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳገጠመው፤ በ2016 ዓ.ም በተመሳሳይ ምክንያት ያጋጠመው ኪሳራ አንድ ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል። የስርቆት መጠኑ ከባለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ እያደገ መምጣቱን እንዲሁም ስርቆት የማይፈጽማቸው አዳዲስ ቦታዎችም ላይ ጭምር እየተከሰተ መሆኑን ተናግረዋል። ችግሩ እንደሀገር የተያዘውን የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት የማስፋፋት እቅድ ፈተና ላይ ጥሎታል ብለዋል።
የብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች የሚገዙትን ብረት መነሻ ሳያጣሩ መግዛታቸው ለመሠረተ-ልማት ስርቆት መባባስ ዋናው ምክንያት እንደሆነ አመልክተው፡- ፋብሪካዎቹ ምንም እንኳን በአሠራር መመሪያቸው ላይ የኤሌክትሪክ ኃይልን፣ የቴሌንና የባቡር ሐዲድን ብረቶች አንቀበልም የሚል መርሕ ቢኖራቸውም፤ ከተቋሙ መሠረተ-ልማቶች የሚሰረቁት ብረቶች ግን እየተቆራረጡና ቅርጻቸው እየተቀየረ መዳረሻቸው ብረት ማቅለጫ ፋብሪካዎች እንደሆነ መረጋገጡን ገልጸዋል።
ጉዳዩንም ፖሊስ እንዲያውቀውና አስፈላጊውን የክትትል ሥራ እንዲሠራ ስለመደረጉ አቶ ሞገስ ጠቁመው፤ ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች በወረቀት ላይ ላስቀመጡት አሠራር ቢገዙ፣ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት በዚህ ልክ ጉዳት ሊደርስበት እንደማይችል አስታውቀዋል ።
ተቋሙ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አደጋውን ለመቀነስ የሚያስችል ጥናት እያስጠና እንደሚገኝ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ማዕከልም አስፈላጊውን የክትትል ሥርዓት እንዲዘረጋ የሚያስችል እቅድ ስለመነደፉ ገልጸዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ስርቆት በሚዘወተርባቸው አካባቢዎች በመገኘት ከላይኛው እስከ ታችኛው መዋቅር ካሉ የመስተዳድርና የፀጥታ አካላት ጋር በችግሩ መንስዔ እና መፍትሔው ላይ ውይይቶች ሲደረጉ እንደነበርም አስታውሰዋል። ሕዝቡን የማስገንዘብ ሥራ ሲሠራ እንደነበርም አስረድተዋል።
ይህ በሂደት ለውጥ ያመጣል ተብሎ ቢታመንበትም አሁን ላይ ብዙ አውድመው ጥቂት ማግኘት የሚፈልጉ የልማት ጸሮች ፈጥነው ከድርጊታቸው ባለመታቀባቸው ችግሩ እየከፋ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ አጥፊዎች ለሕግ ሲቀርቡ ካጠፉት ጥፋት ጋር የሚመጣጠን አስተማሪ ቅጣት እንደማይጣልባቸው አመልክተዋል።
የኤሌክትሪክ ምሰሶ ቆርጠው ጥለውና ዘርፈው ሲያበቁ ሁለት ዓመት ብቻ ታስረው የሚወጡበት፤ አንዳንዴም በአነስተኛ የገንዘብ ቅጣት የሚለቀቁበት ሁኔታ እንዳለ አመልክተው፤ እንዲህ አይነቱ ቅጣት ወንጀል ፈጻሚዎችን ከድርጊታቸው እንደማያርማቸው አስታውቀዋል።
ተቋሙ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶችን በልዩ ሕግ ከማስጠበቅ አንጻር ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ፊሊፒን እና ሌሎች ሀገራት ተግባራዊ ያደረጓቸውን ከባድ ቅጣት የሚያስከትሉ ሕጎችን በመፈተሽ እና በመቀመር አጥፊዎች የሚታረሙበት ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ እያስጠና መሆኑን ጠቁመዋል።
አጥፊዎች በኅብረተሰቡ ጉያ ውስጥ ያሉና ከሕዝብና ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ርካሽ ጥቅም የሚያስቀድሙ፤ በሽርፍራፊ ሳንቲሞች የሚታለሉና ነገዎቻቸውን አሻግረው የማይመለከቱ ናቸው ያሉት አቶ ሞገስ፤ እነዚህን ግለሰቦች ኅብረተሰቡ አጋልጦ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም