የዘርፉን ብልሽት ፈር ለማስያዝ አስፈላጊ የሆነው የስፖርት ሕግ

ዜና ትንታኔ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ስፖርት ከፍተኛ አለመግባባትና ውዝግቦች እየተስተዋሉ ይገኛሉ። ባለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች የነበሩት እሰጣ ገባዎች ደግሞ በተለየ ሁኔታ ማሳያ ይሆናሉ። በስፖርት ማኅበራት እና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተፈጠሩ አለመግባባቶች እንዲሁም አትሌቶች የሚያሰሟቸው አቤቱታዎች ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ስፖርቱን ከሚመራው መንግሥታዊ ተቋም በላይ ሆነው መታየታቸውም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

የሌሎች ሀገራት ልምድ እንደሚያሳየው ከሆነ መሰል ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የሚፈቱበትና ስፖርተኞችም ፍርድ የሚያገኙበት የስፖርት ሕግ ማሕቀፎች መኖራቸውን ነው። ቅሬታቸውን አቅርበው እልባት ካላገኙ ደግሞ ጉዳያቸውን እስከ ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (CAS) ሊያደርሱ ይችላሉ።

ይህ ዓይነቱ አሠራር ለኢትዮጵያም አስፈላጊ ስለመሆኑ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። በኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ‹‹ሃገራዊ የስፖርት ልማት ስብራቶችን በሳይንሳዊ ጥናት እንፍታ›› በሚል መርሕ የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎችም ይህንኑ የሚያመላክቱ ሆነው ተገኝተዋል።

ሰነዱ የሕግ ማሕቀፎችን በሚመለከት ስፖርቱ ግልጽ ተዋረዶችን፣ የተገለጹ ሚናዎችን፣ ኃላፊነቶችን እና ግልጽ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችን ማካተት በዋነኛነት በአማተሩ ሚና እና በባለሙያው መካከል እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል።

ሃገሮች ከዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (CAS) ጋር አብረው የሚሠሩ የየራሳቸውን ብሔራዊ የሕግ ማሕቀፍ ማዘጋጀት እንዲሁም የግልግል አካላት ወይም ፍርድ ቤቶችን ማቋቋም ይችላሉ።

ይህም ብዙውን ጊዜ የፍርድ ቤቱን ወሰን፣ ሥልጣንና አሠራር የሚወስኑ የተወሰኑ ሕጎችን (ደንቦችን) ማውጣትን ያካትታል። በመሆኑም ጥናቱ ብሔራዊ የስፖርት ተቋማትን የሚመሩ የቁጥጥር ሕጎችና ማሕቀፎች መዘጋጀት እንዳለበት አሳስቧል።

በስፖርቱ እየታየ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም ከዘርፉ ልዩ ባሕሪ አንጻር የስፖርት ሕግ እና ገላጋይ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ መኖሩ አስፈላጊ ስለመሆኑ በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የስፖርትና ሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ሃብታሙ ደመላሽ (ዶ/ር) ያብራራሉ።

የስፖርት ሕግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ስላለው ሃገራት ዓለም አቀፉን የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት መሠረት አድርገው የሚተገብሯቸውን የስፖርት ሕግ አዘጋጅተው መጠቀም ከጀመሩ መቆየታቸውን ተሞክሯቸው ያሳያል። ሕጉ መኖሩን ተጠያቂነትን የሚያሰፍን በመሆኑ በስፖርቱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል።

ሌላኛው የስፖርት ሕግ አስፈላጊነትን የሚያንፀባርቁት ኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታምራት በቀለ ናቸው። ቀድሞ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያገለገሉ በመሆናቸው በቅርቡ ብሔራዊ የስፖርት ማኅበራት፤ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ላይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ በነበረው አቤቱታ ላይ ተሳትፈዋል።

ከዚህ ቀደም ሃገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራትን ስለማቋቋምና ስለመወሰን የወጣው መመሪያ ችግሮች ሲኖሩ በመጨረሻ በሃገሪቷ ሕግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል የሚጠቁም በመሆኑ በርካታ ስፖርታዊ አለመግባባቶች ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት ማምራታቸውን ያስታውሳሉ። የስፖርት ፍርድ ቤቶች ቢኖሩ ግን በቀላሉ መፍትሔ ለማግኘት ስለሚቻል በኢትዮጵያ የስፖርት ሕግ ማሕቀፎች እንዲኖሩ መደረጉ ለስፖርቱ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ያምናሉ።

ይህም ብቻ ሳይሆን ስፖርቱን በሚመራው አካል ሕግና ሥርዓትን በማስከበር በኩል የሚስተዋለውን ክፍተት በማሻሻልም የራሱ ሚና ይኖረዋል። ስፖርቱ ፖሊሲና መመሪያ ይኑረው እንጂ ተግባራዊ የሚያደርግ አዋጅ ግን አልነበረውም።

ይህም ዘርፉን የሚመራው አካል አፈጻጸም በሚፈለገው ልክ እንዳይሆንና በአንዳንድ ሂደቶችም ላይ የራሱን ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ነበር። ስለዚህም አስገዳጅ አዋጆች መኖራቸው የስፖርት ማኅበራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ላይ መሻሻሎችን ሊያስከትል ይችላል።

የስፖርት ቤተሰቡን የሚያስማማው የስፖርት ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ ራሱን የቻለ ሂደት ይኖረዋል። በዚህም ላይ የስፖርት ምሑሩ ሃብታሙ (ዶ/ር) እይታ በመሠረታዊነት ሁለት ጉዳዮች አስፈላጊ መሆናቸውን ነው። ቀዳሚው የሕግ ባለሙያ ሲሆን፤ የትኛውም ሕግ ከሚዘጋጅበት ሃገር ሕገ መንግሥት ጋር የሚናበብና የማይጣረስ እንደመሆኑ ሕግን ሊተረጉም የሚችል ዕውቀት ያለው ሰው አስፈላጊ ነው።

ሌላኛው ደግሞ ስፖርቶች ሁሉ የሚተዳደሩበት የየራሳቸው ሕግ ያላቸው ቢሆንም በወጥነት ሙያተኞችንና ሙያውን ሊገዛ የሚችል ማሕቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያን ማካተት አለበት። በዚህም ሁለቱን አካላት የያዘ፣ ገለልተኛ፣ ራስ ገዝ፣ ተጠያቂነት ያለበት፣ አቅዶ የሚሠራና በሃገሪቷ የሚታየውን የስፖርት ምስቅልቅል ሊፈታ የሚችል ተቋምም ሊዋቀር ይገባል።

ይህንንም ለማድረግ ዓለም አቀፉን የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ሕጎችን መመልከት፣ አወቃቀሩንና የሚያካትታቸውን ጉዳዮች ማጥናት እንዲሁም በአፍሪካ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸውን ሃገራት መነሻ በማድረግ መተንተን ቀዳሚው ጉዳይ መሆን አለበት። በምን መልኩ ወደ መሬት መውረድ አለበት የሚለው ሥራ የሚፈልግ እንደመሆኑ የመንግሥት ኃላፊነት ይሆናል።

ስፖርቱን የሚመራው መንግሥታዊ ተቋም ቁርጠኝነቱን ማሳየትና በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት አያጠያይቅም። ነገር ግን የስፖርት ሕግ ማሕቀፍ መዘጋጀት ለስፖርቱ እድገት አንድ እርምጃ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን በስፖርቱ ለረጅም ዓመት ያገለገሉት አቶ ታምራት ያነሳሉ።

ስጋታቸው ደግሞ ስፖርቱን የሚመራው የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በተደጋጋሚ የሚነሳበት የማስፈጸም ችግር ነው። ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ከሚታየው ክፍተት አንጻር በጥናቱ የተመላከቱ ነጥቦችን ሥራ ላይ ለማዋል መሥራት ተገቢ ነው።

ይህ ካልሆነ ግን በቅርቡ ከስፖርት ማኅበራት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ራሱ ወደመደበኛው ፍርድ ቤት ማምራቱ ማሳያ ነው። ስለሆነም መሰል ጉዳዮች ሲገጥሙት መመሪያዎቹን በአዋጅ ደግፎ በራሱ ሊጨርስ ይገባል።

ጥናቱ በርካታ ጉዳዮችን አመላካች እንደመሆኑ በዘርፉ ያሉ አንገብጋቢ ችግሮችን ለመፍተት እንዲሁም የተዝረከረኩ አሠራሮችን ፈር ለማስያዝ ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል። በመሆኑም ባለሙያዎች ተቀራርበውና የሚመለከታቸው ሁሉ ሚናቸውን ተረድተው በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም የስፖርት ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You