አዲስ አበባ፡- የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ተከፈተ ማለት የውጭ ባንኮች ሀገር ውስጥ ገብተው እንደፈለጉ ይሠራሉ፤ የባንኩን ዘርፍ ያጥለቀልቃሉ ማለት እንዳልሆነ የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ አቶ ማሞ ምሕረቱ አስታወቁ። የሀገሪቱ ባንኮች ካፒታላቸውን እያሳደጉና አቅማቸውን እየገነቡ መሄድ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው እለት የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅን ባፀደቀበት ወቅት፡- የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ አቶ ማሞ ምሕረቱ እንዳመለከቱት፤ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ተከፈተ ማለት የውጭ ባንኮች ሀገር ውስጥ ገብተው እንደፈለጉ ይሠራሉ፤ የኢትዮጵያን የባንክ ዘርፍ ያጥለቀልቃሉ ተብሎ መታየት የለበትም ብለዋል።
የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የማድረጉ ጉዳይ ከሦስት ዓመት በፊት ለውይይት ቀርቦ ውሳኔ የተሰጠውና በፖሊሲ የተደገፈ መሆኑን አስታውሰው፣ የአዋጁ መፅደቅ ለሀገር ውስጥ ባንኮች በጎ አስተዋፅዖ እንጂ ተፅዕኖ እንደማይኖረው፤ ይልቁንም ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር በሽርክና የመሥራት፣ የእንደራሴ ቢሮ እና ቅርንጫፎችን የመክፈት ሥራዎችን በማከናወን የራሳቸውን አስተዋፅዖ ያበረክታሉ ብለዋል።
የውጭ ባንኮች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የብድር እና የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማስፋት ማክሮ ኢኮኖሚውን የሚያረጋጉ ስለመሆናቸው ጠቁመው፤ በዚህም የኢትዮጵያ ባንኮች የበለጠ የመጠንከር፣ የመጎልበት እና የመፈጸም አቅም ያገኛሉ ነው ያሉት። የሀገር ውስጥ ባንኮች አስተዋፅዖም ከምንጊዜውም በላይ እንዲያድግ አስተዋፅዖዋቸው ከፍያለ መሆኑንም ገልጸዋል።
የውጭ ባንኮች ሥራ ጀመሩም አልጀመሩም የኢትዮጵያ ባንኮች ካፒታላቸውን እያሳደጉና አቅማቸውን እየገነቡ መሄድ እንዳለባቸው ያመለከቱት የባንኩ ገዥ፣ ኢኮኖሚው እያደገ በመሆኑ የሀገር ውስጥ ባንኮች እርስ በርሳቸው እየተቀናጁ ሀብታቸውን እና አቅማቸውን አሰባስበው የመሥራት ኃላፊነት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
አዋጁ ያስቀመጠው የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩበትን አሠራር፤ እና አካሄድ የሚደነግግ ነው፤ ይህን ተከትሎ ዝርዝር መመሪያዎች በሂደት እንደሚኖሩ አመልክተው፣ አዋጁ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያስፈልጉ ጠንካራ ባንኮች እንዲኖሩና እነዚህንም በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል።
በባንክ ሃብት በተቀማጭ ገንዘብ፣ በብድር እና በካፒታል እያደጉ የመጡ የኢትዮጵያ ባኮችን የበለጠ እንዲጎለብቱ ለማድረግ አዋጁ የሚረዳ ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያስመዘገበ ያለውን እድገት ለማስቀጠል፤ በባንኮች ላይ ቀውስ ሲፈጠር እልባት ለመስጠት፤ የባንክ ዘርፍ የፈቃድ አሰጣጥና የቁጥጥር ማሕቀፍ ከዓለም አቀፍ አሠራር ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማስቻል ያግዛል ብለዋል።
የባንክ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ሆኖ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ያላቸው ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያስችል እና ዘርፉ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያበረታታ መሆኑንም አመልክተዋል። ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን፣ አዋጅ ቁጥር 1360/2017 ሆኖ በሦስት ተቃውሞና በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።
በእለቱ ምክር ቤቱ ስለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል። አዋጁ፤ ብሔራዊ ባንኩ በየጊዜው ከሚስተዋሉ ለውጦች ጋር ራሱን እንዲያጣጥም፤ ማክሮ ኢኮኖሚውን የማረጋጋት ተልዕኮው በአግባቡ እንዲወጣ፤ ምርታማነትን እንዲያሳድግ፤ የኢኮኖሚውን እድገት እንዲያሻሽል፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙን እንዲያስቀጥል፤ እና ሁሉንም የልማት ተዋናዮች ያሳተፈ እንዲሆን የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም