አዲስ አበባ፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመድኃኒት አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት ሰባት አዳዲስ መድኃኒት ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን በኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጨንቻ መላው ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በኩል በየወረዳው አንድ የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት ለመክፈት ታቅዶ እስከ አሁን ሰባት መድኃኒት ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ከሰባቱ አዳዲስ መድኃኒት ቤቶች በተጨማሪ ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት አቅዶ ከቀይ መስቀል መድኃኒት ቤት ጋር ውል መግባቱን አውስተው፤ ሆስፒታሎች መድኃኒት ሳይኖራቸው ሲቀር በየሆስፒታሎች በር አካባቢ የቀይ መስቀል መድኃኒት ቤቶች ተከፍተው ለአባላት መድኃኒት በነፃ እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
አያይዘውም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በመንግሥት ጤና ተቋማት መድኃኒቶች እና ምርመራዎች በማይኖሩበት ጊዜ አባላት ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን በመረዳት ከግል መድኃኒት ቤቶች አገልግሎቱን የሚያገኙበት ሁኔታ ለመፍጠርም የሚያስችል ጥናት እየተደረገ እንደሆነ አውስተው፣ ከ2018 ዓ.ም. በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ጨንቻ መላው በኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በ2006 ዓ.ም. የተከፈተ መሆኑን አስታውሰው፣ በዚሁ ወቅት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን (ማአጤመ) በሙከራ ደረጃ አንድ ወረዳ ላይ እንደ ተጀመረ፣ ከዚያም ወደ ሌሎች ወረዳዎችና ዞኖች እየሰፋ መሄዱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ በአስራ ሁለቱም ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 96 የገጠር ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ጽሕፈት ቤቱ ባከናወነው ከፍተኛ ጥረት ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ ተግባራዊነቱን ማረጋገጥ እንደተቻለም አስረድተዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በተሠራ ጠንካራ ሥራም እስከ 898 ሺህ 535 የሚደርሱ እማ/አባወራዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አባል በማድረግ ከ387 ሚሊዮን 981ሺህ 154 ብር በላይ በመሰብሰቡን ገልጸዋል።
እስካሁንም በጤና መድኅን ሽፋን ስር የሕክምና አገልግሎት ለሰጡ የጤና ተቋማት ከ289 ሚሊዮን 559ሺህ 079 ብር በላይ መክፈል ተችሏል ብለዋል።
የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጨንቻ መላው በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በኩል ከየወረዳዎቹ አብነት በመውሰድ የተጠቃሚዎች እርካታ በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ ከ74 እስከ 80 በመቶ ባለው መሐል ውጤቱ እንደሚሳይ አውስተው፤ አባላቱ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም አገልግሎቱ በጣም ጠቃሚና አዋጭ ነው ማለታቸውንም አንስተዋል።
ስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም