የፍራፍሬ ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ

ዜና ሐተታ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በአሁኑ ጊዜ ከ80 በላይ ባለሀብቶች በግብርና በመሠማራት አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረት ላይ ይገኛሉ። በዞኑ ለግብርና ሥራ የሚሆን ከ438 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ሲኖር፤ ከዚህ ውስጥ 134 ሺህ ሄክታር መሬት እየለማ ነው። ቀሪ ሊለማ የሚችል ከ300 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት መኖሩን የክልሉ ግብርና መረጃ ያሳያል።

ይህ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም ከአካባቢው ማኅበረሰብ አልፎ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚመጡ ዜጎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። በአሁኑ ጊዜ በዞኑ ከተሠማሩ ከ80 በላይ አልሚዎች መካከል በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የሚገኘው ፍርኤል ኢትዮጵያ ድርጅት ተጠቃሽ ነው። የፍርኤል ኢትዮጵያ እርሻ ልማት የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል።

በዋናነት ደግሞ የሙዝ ምርት የሚያመርት ሲሆን ይህን ምርቱንም ወደ ሶማሊላንድ ይልካል። ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ከአራት ሺህ 500 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ለሀገሪቱንም የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ነው። በቀጣይ የእርሻ ሥራዎች በማስፋት ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን ድርጅቱ ይገልጻል።

ወጣት እሥራኤል ኃይሉ በፍርኤል ኢትዮጵያ ድርጅት ውስጥ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች አንዱ ነው። ወጣቱ በመካኒካል ምሕንድስና የተመረቀ ሲሆን በፍርኤል ኢትዮጵያ ድርጅት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በንድፈ ሀሳብ የሚያውቀውን ወደ ተግባር እንዲቀይር ዕድል ተፈጥሮለታል። ገቢው በየጊዜው እያደገ በመንጣቱ ከራሱ አልፎ ቤተሰብ እየረዳ መሆኑን ገልጿል። ድርጅቱ ለተማሩና ላልተማሩ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን በመግለጽ፤ መሰል ድርጅቶች ቢበዙ የሥራ አጥ ቁጥር እንደሚቀንስ ይገልጻል። ወጣቶችም ያገኙትን ሥራ ጊዜና ቦታ ሳይመርጡ መሥራት እንዳለባቸው ምክሩን ለግሷል።

ፍርኤል ኢትዮጵያ ሰፊ እርሻ በማልማት የሀገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ እገዛ እያደረገ ነው የሚለው ወጣቱ፤ በሰፋፊ ድርጅቶች ውስጥ መሥራት ሙሉ እውቀት ለማግኘት ይረዳል። አሁን ላይ የድርጅቱን ማሽኖች ችግር ሲገጥማቸው የማስተካከል እውቀት አግኝቻለሁ። እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያገኘሁትን የንድፈ ሀሳብ እውቀት ወደ ተግባር እንድቀይር አስችሎኛል ብሏል።

የፍርኤል ኢትዮጵያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ረድኤት አፈወርቅ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ አትክልትና ፍራፍሬን በማምረት ለውጭና ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ነው። እንዲሁም አስር ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። የሙዝ ምርት ከፍተኛ ደረጃ የሚይዝ ሲሆን ጥጥ በሁለተኛ ደረጃ እያመረተ ነው። እንዲሁም ማሾ፣ ሰሊጥ፣ ፓፓያ፣ ሀባብ፣ ሱፍና መሰል ሰብሎችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል። የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድም ትልቅ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከሁሉም የሀገሪቷ ክፍሎች የተውጣጡ ከአራት ሺህ 500 በላይ ሠራተኞች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ረድኤት፤ ድርጅቱ ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘቱም በላይ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ወደፊትም የእርሻ ሥራውን በማስፋፋት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠራል ነው ያሉት።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በፍርኤል ኢትዮጵያ ሰባት አይነት የሙዝ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን ዝርያዎች ከእሥራኤልና ከኮስታሪካ የሚመጡ ናቸው። በ2017 ዓ.ም ብቻ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ችግኞችን ወደ ሀገር በማስገባት የተከላ ሥራ ተከናውኗል። በአንድ ሄክታር ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ችግኞች ይተከላሉ። እንዲሁም በሀገር ውስጥ ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ድርጅቱ ወደ ፊት በሙዝ ምርት በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሠራ ነው። ከሶማሊላንድ በተጨማሪ ለመካከለኛው ምሥራቅና ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብ ለሙከራ የሚሆን ምርት መላኩንም ገልጸዋል።

ፍርኤል ኢትዮጵያ ድርጅት ራሱን ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር አዛምዶ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ረድኤት፤ የሙዝ ምርት ከማሳ ወደ ማሸጊያ እስኪደርስ ድረስ ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከሰዎችን ንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ የሚካሄድ መሆኑን ይገልጻሉ። ድርጅቱ ለሀገር እያስገኘ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ መንግሥት የኤሌክትሪክና የመንገድ የመሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ ሲሉ ጠይቀዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ አቶ ሰይፉ አየለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ዞኑ ለግብርና ሥራ የሚውል ሰፊ መሬት አለው። ነገር ግን አሁን ላይ 134 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ አልሚዎች እያለሙ ይገኛሉ፤ ከዚህ ውስጥ ፍርኤል ኢትዮጵያ 10 ሺህ ሄክታር መሬት ወስዶ ሙዝንና ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎችን እያለማ ነው። ለብዙ የአካባቢው ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ሙዝን ከሀገር ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ነው ብለዋል።

በዞኑ 80 የሚደርሱ አልሚዎች አሉ ያሉት ኃላፊው፤ ክልሉ በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ በርካታ አልሚዎች ወደ ዞኑ እየመጡ ነው። በ2017 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ተጨማሪ 20 አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል። ለአካባቢው የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዞኑ ያሉ ባለሀብቶች ወደ 6 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት ማካሄዳቸውን በመግለጽ፤ ሙዝና ሃባብ ወደ ሶማሊላንድ በቀጥታ እንደሚላክም ገልጸዋል።

ሞገስ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You