በአካል ጉዳት የሕክምና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ወጥ የሆነ መመሪያ የለም

አዲስ አበባ፡- በሕክምና ምስክር ወረቀት አሰጣጥ ዙሪያ ወጥ የሆነ አዋጅም ሆነ መመሪያ እንደሌለ የዳግማዊ ምኒሊክ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ። ችግሩ ዶላር ለማግኘት ሲባል ሀገር ውስጥ መታከም የሚችሉ ሕሙማንን ወደ ውጭ ሀገር ሂደው እንዲታከሙ እያደረገ መሆኑን ጠቆመ።

የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ተከተል ጥላሁን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ከሀገር ውስጥም ሆነ ሀገር ውጭ ለሆነ ሕክምና የሚሰጥ የሕክምና ማስረጃ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ አሠራር አለው። በእኛ ሀገር ግን ወጥ የሆነ አዋጅም ሆነ መመሪያ የለም።

ማንኛውም ሰው ለአካል ጉዳት የሚሰጥ የምስክር ወረቀት (የሕክምና ማስረጃ) የማግኘት መብት እንዳለው ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ፣ ማስረጃው ማንኛውም ሰው ታክሞ ስለበሽታዬ ማስረጃ ይሰጠኝ ብሎ ሲጠይቅ በጽሑፍ ወይም በማብራሪያ መልኩ የጉዳት መጠኑን ጨምሮ የሚሰጠው ማስረጃ ነው ብለዋል።

የቦርድ የሕክምና ማስረጃ ይሰጠኝ ጥያቄ  ግን ለውሳኔ በቦርዱ የሚሰጥ ነው፣ በፍርድ ቤት ታዞ ተጎጂው የደረሰበትን የጉዳት አይነት፣ ጉዳቱ ዘላቂ ይሁን ጊዜያዊ ባለው የጉዳት መጠን በመቶኛ ተገልጾ የሚሰጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።

እንደ ዶክተር ተከተል ገለጻ፤ የጉዳት የምስክር ወረቀት በፍርድ ቤት አሊያም ወይም የተጎዳው አካል ጥቅም ሊያገኝበት እና ጉዳቱን ሊያካክስለት የሚችለው መሥሪያ ቤት ሲጠይቅ የሚሰጥ ማስረጃ ነው። አሰጣጡም ሦስት ሐኪሞች እያንዳንዷን የጉዳት ዓይነትና መጠን መርምረው በመቶኛ አውጥተው በሆስፒታሉ የበላይ ኃላፊ ተረጋግጦ ለጠየቀው አካል የሚሰጥ መረጃ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

ታካሚው የጉዳት መጠኔን ይዤ ልክሰስ ካለ ለራሱ የሚሰጥ ሰርቲፊኬት እንዳለ የጠቆሙት ዶክተር ተከተል፤ የቦርድ የሕክምና የምስክር ወረቀት የሚሰጠው ተቋማት የራሳቸው አሠራርና ደንብ ስላላቸው ቦርዱ ለግለሰቡ መረጃ አይሰጥም ብለዋል።

ድርጅቶች የራሳቸውን ጥቅም የሚጎዳ ከሆነ መረጃ ስጡት ብለው ላይጠይቁ ይችላሉ። ነገር ግን ድርጅቱን የመክሰስ መብት የተጎጂው አካል በመሆኑ በክስ ወቅት ካቀረበ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሕክምና ቦርዱ ጽፎ እንደሚሰጥ ዶክተር ተከተል ተናግረዋል።

ከሀገር ውስጥም ሆነ ሀገር ውጭ ለሆነ ሕክምና የሚሰጠው የሕክምና ማስረጃ የሚሠራበት አሠራር አለው የሚሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ እያንዳንዱ አካል ክፍል ላይ በሚደርስ ጉዳት የሚጻፍ ዓለም አቀፍ የሕክምና ሕግን የተከተለ አሠራር አለ። ይህ ሆኖ ግን የሕክምና ማስረጃ አሰጣጡ በተቋማት የውስጥ አሠራር እንጂ በአዋጅም ሆነ ወጥ በሆነ መመሪያ የሚመራ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።

የሕክምና ሥርዓቱ አላግባብ ጥቅም ላይ ከሚውልበት ሥርዓት አንዱ ቦርድ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ተከተል፤ ከሚገጥማቸው ፈተና አንዱ ሀገር ውስጥ መታከም የሚችሉትን ዶላር ለማግኘት ሲባል ወደ ውጭ ሀገር ሂዶ ለመታከም ያልተገባ ነገር የሚሠራበት ነው። በየሆስፒታሎች የሚሠራውን ሥራ በአንድ ማዕከል ሜዲካል ቦርድ ተቋቁሞ ሊሠራበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You