አዲስ አበባ፡- እንደ አገር የመጠጥ ውሃን ማዳረስ ፈተና የሆነብን በመረጃና በተጨባጭ በከተሞች ያለው የነዋሪ ቁጥር ባለመመጣጠኑ እንደሆነ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አስታወቁ። ሰው በቤቱ የሚጠቀመውን ውሃ ካልቆጠበና የሚያመርተውን ብሎኬትም ሆነ የከተማ ግብርና ሥራውን በዝናብ ውሃ ካላለማ በስተቀር ንጹሕ የመጠጥ ውሃን በአግባቡ ማዳረስ አዳጋች እንደሆነ አመለከቱ።
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ እንደ ሃገር የመጠጥ ውሃን ማዳረስ ፈተና የሆነብን የውሃው መጠንና የሰው ቁጥር አለመመጣጠን ላይ ነው። በመረጃ ያለን የሰው ቁጥርና በተጨባጭ ከተማ ውስጥ ያለው የሰው ቁጥር አንድ አይደለም።
አንድ ከተማ ተወስዶ ዲዛይን በሚደረግበት ጊዜ ነዋሪው 20 ሺህ ነው ከተባለ ውሃ የሚዘጋጀው ለ20 ሺህ ነዋሪ ነው ያሉት ኢንጂነር ሀብታሙ፣ በተጨባጭ የሚገኘው የሰው ቁጥር ግን 30 ሺህ እና 40 ሺህ ሆኖ የሚገኝበት ሁኔታ ይከሰታል ብለዋል።
ሚኒስትሩ፣ ትክክለኛው የሕዝብ ቁጥር ስለማይታወቅም ውሃው በተመረቀ ማግስት ውሃ የለም እንደሚባል ጠቅሰው፤ መሬት ላይ ያለው የሰው ቁጥርና በመረጃ ያለው የሰው ቁጥር ልዩነቱ የሰማይና ምድር ያህል ነው ብለዋል። ይህም በመሆኑ የውሃ አቅርቦቱን ሥራ ፈታኝ አድርጎት መቆየቱን አስረድተዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፡- የውሃ እጥረት እንዲፈጠር ካደረጉት መካከል የውሃ ብክነት ሌላው ተጠቃሽ ነው። ሰው በቤቱ የሚጠቀመውን ውሃ ካልቆጠበ በስተቀር በሰው ልክ ተቆጥሮ የመጣውን ውሃ በአግባቡ ማዳረስ አይቻልም። ብዙዎች ለፕሮጀክቶቻቸው ለምሳሌ ለብሎኬት ማምረቻም ሆነ ሌላው ቀርቶ ለከተማ ግብርና አገልግሎት የሚያውሉት ውሃ የቧንቧ ውሃን ነው። ለእነዚህ መሰል አገልግሎት ማዋል የሚጠበቅባቸው በዝናብ ወቅት ደጃቸው ላይ የሚዘንበውን ውሃ በአግባቡ በመያዝ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የፖለቲካ አመራሩ፣ የከተማ ከንቲባ ወይም የዞንና የወረዳ አመራሩ ስለ ውሃ የሚያወሩት ሲጠፋ ብቻ ነው። ቀድመው ችግሩን ለመፍታት በጀት አይመድቡም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከተሞች ለወጪዎቻቸው በጀት እንደሚመድቡ ሁሉ ለውሃም በጀት ሊመድቡ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
ለምሳሌ መንገድን በጌጠኛ ድንጋይ (ኮብል ስቶን) ለመሥራት በጀት ይመድባሉ። ለጎርፍ መከላከል በሚልም በጀት መድበው ይንቀሳቀሳሉ። ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ ይመድባሉ። ለውሃ ግን በጀት አይመድቡም ሲሉም አመልክተዋል።
ውሃ ሳይኖር መንገድ አይኖርም። ውሃ ሳይኖር ሌላ ነገር አይታሰብም። ይህ በከተማ ደረጃ፣ በወረዳ ደረጃ በአንዳንድ ክልሎች ጭምር ባለቤት ያለመሆን ጉዳይ ይታያል። ይህ ግን መሆን እንደሌለበት አስገንዝበዋል
ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ለአንድ ከተማ የሚመጣው ትልቅ ዋጋ ተከፍሎ ነው። በተለይም በማጣራትም በማጓጓዝም ደረጃ ቀላል የማይባል ዋጋ ይከፈላል። ይህ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ንጹሕ ውሃ መኪናዎችን ማጠብን ማቆም እንዳለበትም አስታውቀዋል።
የመጠጥ ውሃን በተገቢው መንገድ መጠቀም የማይቻል ከሆነ፣ ውሃው ሕዝብ ዘንድ በተገቢው መንገድ እንዳይደርስ ጫና ይፈጥራል ብለዋል። ሕገ ወጥ ግንባታም የውሃ እጥረትን የሚፈጥር በመሆኑ ከዚህ አይነት አካሔድም መቆጠቡ ጫናን የሚቀንስ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፡- ሌላው የውሃ ብክነት ናቸው ከሚባሉት ውስጥ በየቦታው ቧንቧ ፈንድቶ እየፈሰሰ መዋሉ ነው። ይህ የውሃ እጥረትን ያመጣል። ይህ አይነቱ ጉዳይ የከተማ፣ የዞንና የወረዳ አመራሩን ትኩረት የሚሻ ነው። እንደማንኛውም ሥራ ተከታትሎ ውሃ ከተመረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከሚሸጥ ድረስ መከታተልና ወደ ገንዘብ መቀየር ድረስ የሁሉንም ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ያጠፋውን አካል ከመቅጣት ጀምሮ ቁርጠኛ መሆንን የሚጠይቅ ነው። ሚኒስቴሩም እንደተቋም የጀማመራቸው ሥራዎች ያሉ ሲሆን የድርሻውን እንደሚወጣም አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ፣ የውሃ ሀብት ሲባል ባለቤቱ ሕዝቡ ነው። እሱን መምራት ያስፈልጋል። ውሃን ካልተንከባከብንና ካልጠበቅነው አላቂ እንደመሆኑ እጥረት ያጋጥማል ብለዋል።
በየከተማው ያሉ ጉድጓዶች እየደረቁ መጡ ሲባል የደረቁት ወይ ወደ ጉድጓድ የሚገባ ምንጭ ባለመኖሩ ነው። እሱ ደግሞ የማይኖረው ተፋሰስ ላይ ስለማይሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በአግባቡ ስለማይጠብቁ ነው። አካባቢያቸውን ሕንጻ በሕንጻ ስለሚያደርጉ የሚመጣው የዝናብ መጠን ወደ ከርሰ ምድር መስረጉ ቀርቶ ጎርፍ ይሆናል፡። ከዚህ አኳያ ሁሉም ሰው በየደጁ ውሃን የሚጠብቅበት አሠራር ሊከተልና በያገባኛል መንፈስ ሊንቀሳቀስ ይገባዋል ሲሉ አብራርተዋል።
እንደ ቧንቧ፣ ቦኖ እና የውሃ ግድቦችን ያሉትን ለውሃ መሠረተ ልማቶችን ሕዝቡ እንደራሱ ንብረት ሊጠብቃቸው ይገባል። መሠረተ ልማቱ ሲበላሽ እና ውሃ ሲፈስ እያየ ከሔደ እንዲሁም በቤቱ የሚጠቀመውን ውሃ ካልቆጠበ በሰው ልክ ተቆጥሮ የመጣ ውሃ በአግባቡ መድረስ አይችልምና እጥረት ይፈጠራል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ውሃ እያላት ድሃ የሆነችው ውሃን በቁጠባ ባለመጠቀምና በደጅ ያለውን ውሃ ባለመያዝ መሆኑን መረዳት ይጠበቃል። ውሃ ደጁ ላይ ሲዘንብ ጉድጓድ ቆፍሮ የዘነበውን ውሃ ማቆየት ካልተቻለ ከሦስት ቀን በኋላ ውሃ ፍለጋ መሄዱ አይቀርምና በዚህ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጡ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።፡
እንደ ሃገር በሰው ቁጥር ሲታይ ወደ 71 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆን ሰው የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆኗል። ይህ ቁጥር የከተማውንም የገጠሩንም የሚያጠቃልል ነው። በቂ ነው ወይ ከተባለ የሕዝቡ ቁጥር ስለሚታወቅ በቂ አይደለም ብለዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም