ለኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና ለአደጋ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን የመፍታት ሥራዎች እየተሠሩ ነው

ዛፎች ለኃይል መቆራረጥ 47 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው በጥናት ታውቋል

አዲስ አበባ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ ለኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና ለአደጋ መንስኤ የሆኑ ዛፎችን እየቆረጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፤ በኤሌክትሪክ መስመሮች አቅራቢያ ያሉ ዛፎች ለኃይል መቆራረጥ 47 በመቶ ምክንያት እየሆኑ እንዳሉም በጥናት ተለይቷል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ታየ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከኤሌክትሪክ መስመሮች ጋር ንክኪ ፈጥረው ለኃይል መቆራረጥና ለተለያዩ አደጋዎች መንስኤ የሚሆኑ ዛፎች እየተቆረጡ ነው። ዛፎች እና ግንባታዎች ከኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ከሦስት ሜትር በላይ ርቀው መገኘት እንዳለባቸው የተቀመጠ መመሪያ እንዳለ ጠቅሰው፤ ይህ መመሪያው በአንዳንድ ቦታዎች ተግባራዊ ባለመሆኑ ዛፎች ቅርንጫፎቻቸው እየተንሰራፋ ለኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና ለተለያዩ አደጋዎች መንስኤ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ችግሩ ከግንዛቤ ማነስና ሕግ ከማስከበር ጉድለት እንደተከሰተ አስረድተው፤ ተቋሙ በአንድ በኩል ሚዲያዎችን በመጠቀም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች እየሠራ እንዳለና በሌላ በኩል የአደጋ ስጋት የሆኑ ዛፎችን እየቆረጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መስመሮችን ሲዘረጋ በዘፈቀደ ሳይሆን የከተሞችን ማስተር ፕላን ተከትሎ ነው ያሉት አቶ መላኩ፤ መሠረተ ልማቱ ከተዘረጋ በኋላ የሚሠሩ ግንባታዎች፣ የሚታጠሩ አጥሮች፣ የሚተከሉ ዛፎች ወደ ኤሌክትሪክ መስመሩ ከመጠጋት አልፈው መስመሩ በላያቸው ላይ አቋርጧቸው የሚሄድበት ሁኔታ እንዳለ አስረድተዋል። ይህ ሁኔታ ለኃይል አቅርቦቱ መስተጓጎልና ለአደጋዎች መጨመር ምክንያት እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ችግር የሚፈጠሩ ዛፎችን መቁረጥ አሁን የተጀመረ አይደለም ያሉት አቶ መላኩ፤ አሁን በስፋት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈለገው በኃይል መቆራረጥ ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖው 47 በመቶ በመድረሱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ገና ከጅምሩ በተወሰዱ ርምጃዎችም የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽ በእጅጉ መሻሻሉን ተናግረዋል። የበለጠ ቢሠራበት የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣ ታምኖበት በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ ምሶሶዎችን እና ገመዶችን ተጠግተው የሚፈጸሙ ግንባታዎችም ሥርዓት እንዲይዙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራና በኮሪደር ልማት የሚተከሉ ዛፎችን በተቀመጠው መመሪያ መሠረት ከኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች አርቆ መትከል እንደሚገባም ተናግረዋል። የኮሪደር ልማት ባለባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መስመሮች በመሬት ስር መተላለፍ መጀመራቸውን እንደ ጥሩ መፍትሔ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሙሉ ለሙሉ እዚህ ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ዛፎችን ከኤሌክትሪክ መስመሮችና ምሰሶዎች አርቆ መትከል መረሳት እንደሌለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በርካታ ዛፎችን እንደተከለ ጠቅሰው፤ ዛፎችን የሚቆርጠው የሚያስከትሉትን ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለማስቀረት መሆኑን አስረድተዋል።

በዛፍ ቆረጣው ዘመቻ ብዙኃኑ እየተባበረ እንዳለና አንዳንድ ግለሰቦች ግን ለምን ዛፋችን ይቆረጣል በሚል አምባጓሮ እንደሚያነሱ ጠቅሰው፤ የሚመለከታቸው አካላት ተቋሙ የሚሠራውን ሥራ እንዲደግፉና ሕግ የማስከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አቶ መላኩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You