በቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የተቋቋመው “የአዳም ፋውንዴሽን” ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአዳም ፋውንዴሽን የማብሰሪያ ሥነሥርዓት ትናንት በአዲስ አበባ ሲካሄድ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ባሳለፍኳቸው የመሪነት ዘመን የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ተረድቻለሁ።
በቀጣይ የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን በማስፋፋት ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ብልፅግና የድርሻዬን ለመወጣት ቁርጠኛ ነኝ ሲሉ አስታውቀዋል።
የተመጣጠነ ምግብ ለኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ እድገት ሞተር በመሆኑ የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን ማሳደግ የግድ መሆኑን አመላክተዋል።
በአፍሪካ ያለውን መቀንጨር በመግታት በአዕምሯዊ እና አካላዊ እድገት የዳበረ የሰው ኃይል ለማፍራት ቅድሚያ የሚሰጠው ሥርዓተ ምግብ ተደራሽነት መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትበብር እና በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሕጻናት የተሟላ ስብዕና እና ጤንነት እንዲኖራቸው ከጽንስ እስከ ሁለት ዓመት ባሉት ጊዜያት የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል ነው ያሉት።
የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት የነገ ትውልድን ለማፍራት የርብርብ ማዕከል ናቸው ያሉት አቶ ደመቀ፤ ለሕጻናት አዕምሯዊ እና አካላዊ እድገት የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ መተኪያ የለውም ሲሉ ተናግረዋል።
ለልጆች ጥሩ ትምህርት ቤት የሚያስፈልገውን ያህል የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መሆኑን አስታውቀዋል።
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ጎልቶ እንደሚታይ ገልጸው፤ ችግሩን መፍታት የሚያስችል የአዳም የፋውንዴሽን ተቋቁሟል ነው ያሉት።
ምግብ ማቀነባበር፣ ጤናና ሥርዓተ ምግብን ማሻሻል እንዲሁም ግብርና፣ ትምህርትና ማኅበራዊ ጥበቃ የአዳም ፋውንዴሽን ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፋውንዴሽኑ የአጀንዳ 2063 እቅድን ለማሳካት አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ እና ከሀገራዊ የሌማት ትሩፋት እና ከምግብ ሥርዓት ንቅናቄዎች ጋር የተቆራኘ መሆኑን አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የጤና እና የግብርና ሚኒስቴር እና ሌሎች በርካታ ተቋማት የፋውዴሽኑ አጋሮች መሆናቸውን አመላክተዋል።
ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በቁጥር 7260/24 የተመዘገበ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሆኑ ታውቋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2017 ዓ.ም