በሃይማኖቶች የተወገዘው ሙስና ለምን ፈተና ሆነ?

ጉቦ ማለት መብትን መግዛት ነው ይላሉ። እንደ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን እንደ ስብዕናም ነውር መሆኑን ይገልፃሉ። በሃይማኖቱ የደከሙበትን መስጠት እንጂ ያልደከሙበትን መቀበል አይፈቀድም የሚሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መምህር የሆኑት መጋቢ ሀዲስ ዓለማየሁ እሸቱ፤ ድርጊቱ ወንጀል፣ ርኩሰት፣ የሕዝብና የሀገር ዕድገት ልጓም መሆኑን ይገልፃሉ።

በሠለጠኑ ሀገራት ሙስና የለም ማለት ባይቻልም የሰውን መብት የሚነኩ፣ የሰውን ጤና የሚያቃውሱና የሰውን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚነኩ ጉዳዮች ላይ ግን ሙስና የለም ይላሉ። ያ የሆነው ደግሞ ሕዝባቸው ሃይማኖተኛ ስለሆነ ሳይሆን ጠንካራ ሕግ በመኖሩ ነው የሚሉት መምህሩ፤ የሃይማኖት አባቶች ብቻ ሳይሆኑ መንግሥትም ሕዝቡን ከዚህ እኩይ ድርጊት መጠበቅ አለበት በማለት ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል ሃይማኖቶችስ ይህን እንድንፀየፍ እየነገሩን ነው ወይ?፣ ተሰሚነታቸውስ እስከምን ድረስ ነው፣ የሚናገሩበት ቋንቋ ለሰሚዎቻቸው የሚመጥንና አመለካከታቸውን የሚቀይር ነው ወይ የሚለውን ከእምነት ተቋማት ጋር መነጋገር ያስፈልጋል ይላሉ። መንግሥት ወይም ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ተገናኝቶ መሥራት እንዳለበት ይጠቁማሉ።

የሞራል ልዕልና ካለመኖሩ አኳያ ጉቦ ተቀባዩ ደረቱን ነፍቶ እየሄደ የሚታይበት ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ መንግሥት ሾፌር ነው ማኅበረሰቡ ተሳፋሪ ነውና መንግሥት ጠበቅ ያለ ሕግ ካወጣና የሃይማኖት ተቋማት ጋር ያለው ትምህርት ከተጠናከረ ማኅበረሰቡ ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም ነው ያሉት።

የእስልምና ሃይማኖት መሪ የሆኑት ሼህ ሁሴን አወል የግብረገብ ትምህርቶች በትምህርት ማዕከላት አለመሰጠቱ፣ የሃይማኖት አባቶች በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው አለማስተማራቸው እንዲሁም እንዲህ ያሉ ሰዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ አለመወሰዱ ነው ይላሉ። የእነዚህ ሦስት ነገሮች መላላት ደግሞ ኅብረተሰቡ ድርጊቱን እንዲላመደው አድርጓል የሚሉት የሃይማኖት መሪው፤ ፀያፍ የሆኑ ነገሮች አንድ ተብለው ከተጀመሩ ሁለት ብሎ ለመሄድ በጣም ቀላል ነው ይላሉ።

እንደእስልምና ሃይማኖት አስተምሕሮ ሕዝብን ማገልገል ከፈጣሪው የሚሰጥ ኃላፊነት ነው የሚሉት የሃይማኖት መሪው፤ ጉቦ መስጠትም፤ መቀበልም አስነዋሪ ነው በማለት ያስረዳሉ። ጉቦ ሰጪው ኃላፊነት ላይ የተቀመጠውን ሰው ያሳስተዋል፤ ተቀባዩም ጉቦ ካለ በሚል ፍትሕን የማዛባት ሥራን ይሠራል ይላሉ። የዕድገት ፀር፣ የሠላም ፀር እንዲሁም የፍቅር ፀር ነው በማለት ገልፀው፤ በእስልምና ሃይማኖት የተወገዘ ተግባር መሆኑን ይገልፃሉ።

ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር ሕጋዊ አሠራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለፁት መሪው፤ ማኅበረሰቡ ፈጣሪውን መፍራት እንደሚገባው ይናገራሉ። ጉቦ መስጠትም ሆነ መቀበል የሀገር ኢኮኖሚ እንዲንኮታኮት ያደርጋል፤ ፍቅርን ያጠፋል፤ ስግብግብ ሰዎችን ያበዛል ይላሉ። ከዚህ አኳያም የሚመለከተው ሁሉ ከዚህ ድርጊት ይራቅ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችም ነፍሳቸውን በማሸነፍና ስሜታቸውን በመግዛት ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከባሕላችን፣ ከሞራል እሴቶቻችንና ከሃይማኖቶቻችን አንፃር እንኳ የድርጊቱን ነውርነት፣ አጸያፊነቱና ጉዳቱ ግልጽ በመሆኑ ከወዲሁ አምርረን ልንታገለው ይገባል ሲሉ ነው የሃይማኖት አባቶች ምክረ ሀሳብ የሰጡት።

ነፃነት ዓለሙ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You