ቻይና አረንጓዴ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በንቃት እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፡- ቻይና በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው የአረንጓዴ ልማት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በንቃት እየተሳተፈችና ድጋፍ እያደረገች መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ ገለጹ።

አምባሳደሩ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ ቻይና እኤአ በ2030 የካርቦን ልቀትን ለመቀነስና በ2060 ካርቦን ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተለያዩ ስትራቴጂዎችንና ፖሊሲዎችን ቀርጻ በመተግበር ላይ ትገኛለች። በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ ቀጣይነት ያለው አረንጓዴ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥም በንቃት እየተሳተፈችና ድጋፍ እያደረገች ነው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተነደፈው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም በፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ይፋ ከተደረገው ሥርዓተ ምሕዳርን የጠበቀ እድገት ማ ስመዝገብ ጋር የሚጣጣም መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሁለቱ ሀገራት ቃላቸውን ወደ ተግባር በመቀየር ላይ የሚገኙና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ምሳሌ የሚሆን ሥራ እየሠሩ ነው ያሉት አምባሳደር ቸን፤ የቻይና ባለሀብቶች የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ሲኖ አልሙኒየም ማኑፋክቸሪንግ የተባለው ኩባንያ ፕላስቲክ ተረፈ ምርቶችን ወደ ፋይበር በመቀየር ለተለያዩ ምርቶች ግብዓትነት እንዲውል እያደረገ ነው። በዚህም በሺህ የሚቆጠር ቶኖች ዓመታዊ ምርት ላይ ደርሷል። ኤምባሲውም ሌሎችም የቻይና ኩባንያዎች በአረንጓዴ ዐሻራ ጋር የሚጣጣም ሥራዎች ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እንደሚያበረታታ አብራርተዋል።

የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሠሩ ጠቅሰው፤ ቻይና ቀጣናው ላይ መተማመን ላይ የተመሠረተ አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍንም የበኩሏን አስተዋፅዖ እንደምታበረክትም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ጠንካራ ሠራተኛ ሆነ ሕዝብ እንዲሁም ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር መሆኗን ያስታወሱት አምባሳደር ቸን፤ ይህም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመሠረተ ልማት በሌሎችም ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አመላክተዋል።

እነዚህም በቻይናና በኢትዮጵያ መሪዎች መካከል መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች ወደ ተግባራዊ እርምጃ ለመግባት መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ የቻይና የግብርና ባለሙያዎች ወደኢትዮጵያ መጥተው እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቻይና ቡናን ጨምሮ ወደ ሀገሯ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን እያሳደገች መሆኑን ጠቅሰው፤ የቻይና ባለሀብቶች ማዳበሪያን ጨምሮ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ የሆኑ የግብርና ግብዓቶችን ለማቅረብ እየሠሩ ነው ብለዋል።

በጥቅሉ ቻይና በግብርና ልማት ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ልምድ ስላላት ዋነኛዋ የኢትዮጵያ አጋር ሆና እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በቢሾፍቱ በምትገነባው ግዙፍ የአየር ማረፊያ ግንባታ ላይ ለመሳተፍ የቻይና ድርጅቶች የአዋጭነት ጥናት በማከናወን ላይ መሆናቸውንም አምባሳደሩ ጨምረው ገልጸዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You