ዜና ትንታኔ
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ፣ በጨርቃጨርቅና በሌሎች የኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ላይ በማተኮር መሥራት ከጀመረች ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኢትዮጵያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ በጀመረችው የተኪ ምርት (import substitute) ስትራቴጂ መሠረት 96 ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ማቀዷ ይታወቃል። በዚሁ መሠረትም ባለፈው ዓመት ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ያህል የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
ምርቶች በዋናነት የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤቶች ከፍተኛውን ድርሻ (80 በመቶ) የሚይዙ ሲሆን በዋናነት የምግብ ዘይት፣ ፓስታና አልሚ ምግቦች፣ እንዲሁም የቢራ ብቅል ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ ሀገር የተጀመረው “የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” ምርታማነትን ለመጨመር እና ተኪ ምርቶችን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ማዳን የተቻለው የውጭ ምንዛሪ አመላካች ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስቀሩ መሆኑንም ምሑራኑ ይናገራሉ፡፡
ተኪ የወጪ ንግድ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ዘላቂ ኢኮኖሚን ለመገንባት ምን ፋይዳ አለው? የትኞቹ ተኪ ምርቶች ላይስ ማተኮር ያስፈልጋል? እና በመሰል ጉዳዮች ላይ የምጣኔ ሀብት ምሑራንን አነጋግረን ም ላሽ ይዘናል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገበያ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ብርሃኑ ቡርጂ (ፕሮፌሰር) ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ፋይዳን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሲገልጹ፤ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ሀገሪቷ በውጭ ምርት ጥገኛ እንዳትሆን ያደርጋል ይላሉ፡፡
በሀገር ውስጥ ማምረት እየተቻለ በርካታ ምርቶች ከውጭ ሲገቡ ለሠለጠኑ ሀገራት ጥገኛ መሆንን እንደሚያስከትል የሚገልጹት ፕሮፌሰሩ፤ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሀገሪቷን የኢኮኖሚ እድገት ያሳልጣል። ተኪ ምርቶችን ለማምረት ሲባል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ማሽነሪዎች የሚገቡ በመሆኑ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እንደሚፈጠሩም ይገልጻሉ።
ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት ሲወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስቀር የሚገልጹት ምሑሩ፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት የውጭ ምንዛሪ ጥገኝነትንም ያስቀራል ይላሉ ።
ሀገር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል ባደጉት ሀገራት ላይ ጥገኛ ትሆናለች የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ አብዛኛው የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ማሟላት ከተቻለ የውጭ ምንዛሪ ጥገኝነቱ እንደሚቀንስም ይናገራሉ።
ለአምራቾች የተለያዩ ማበረታቻዎችን በመስጠት አምራቾች ወደ ማምረት እንዲገቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ይህ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እንዲያድጉ በማድረግ ሀገሪቷ በኢንዱስትሪ የበለፀገች እንድትሆን ያደርጋታል ነው ያሉት።
ተኪ ምርቶች እዚሁ በሀገር ውስጥ ጉልበት እና ሀብት የሚመረቱ በመሆኑ ዋጋቸው ከውጭ ከሚመጡ ምርቶች እንደሚቀንሱ የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ፤ ይህ ደግሞ ዋጋን በማረጋጋት የራሱ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ይላሉ።
እንደ ብራዚል፣ ሜክሲኮ እና አርጀንቲና የመሳሰሉ ሀገራት በመጀመሪያ ተኪ ምርቶችን ምግብ ላይ በማተኮር በምግብ እራሳቸውን ለመቻል ነው የሠሩት ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አሁን ላይ ሀገራቱ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችንና ሌሎች ነገሮችን በማምረት ከውጭ የሚያስገቡትን አብዛኛውን ነገር በማስቀረት ሀገራቸውን ማሳደጋቸውን ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያም በቅድሚያ ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮችን በሀገር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንዲመረቱ በማድረግ የሕዝቡን ፍላጎት በማሟላት የተረፈውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ትችላለች የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ከምግብ ፍላጎታችን በራሳችን ኢንዱስትሪ ምርቶች ከሸፈንን በኋላ የኤሌክትሮኒክስ እና ማሽኖችን በሀገር ውስጥ በማምረትም ተኪ ምርቶችን ማሳደግ እንደሚቻልም አመላክተዋል።
እንደ ሀገር አሁን ላይ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ በመልካም ሁኔታ ላይ ነው የሚሉት ምሑሩ፤ በቀጣይም ገጠራማ አካባቢዎች ድረስ በመውረድ መታረስ የሚችል መሬት ሳይታረስ እንዳይቀር መሠራት አለበት ይላሉ።
ኢትዮጵያ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት በኢኮኖሚ እራሷን በመቻል ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ከተላቀቀች ያደጉት ሀገራት በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አይገቡም። ኢትዮጵያ የፀጥታ ሁኔታው ላይ በመሥራት አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠር በማድረግ ምርትና ምርታማነት ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አንድ ሀገር ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሏ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ የጎላ ነው። ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ሲቻል ሀገር የራሷን የሰው ኃይል እና ጥሬ እቃዎች በሚገባ መጠቀም ትችላለች። ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ልምድም ይዳብራል።
ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አስፈላጊነት ብዙ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ተግባራዊነቱ ላይ ያለው አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው ብለው የሚያምኑት አጥላው (ዶ/ር)፤ ተኪ ምርቶችን ማምረት በሚቻለው ልክ ማምረት አለመቻሉ ኢትዮጵያ እስከአሁን ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የአቅም እና የእውቀት ችግር የለባትም የሚሉት ምሑሩ፤ አሁንም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ተነሳሽነቱ መጨመር አለበት። ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የተጀመረው እንቅስቃሴም በቂ ባለመሆኑ ማደግ እንዳለበትም ይናገራሉ።
የምግብ ሸቀጦች፣ አነስተኛ ሸቀጣሸቀጦች እና አልባሳት እዚሁ በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገቡትን ማስቀረት እንደሚቻል ተናግረው፤ ቀስ በቀስ አብዛኛው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት እንደሚቻልም ይገልጻሉ።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ሀገር ውስጥ በሚመረቱ ተኪ ምርቶች መተካት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ምሑራኑ ይስማማሉ። ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትም ፋይዳው የጎላ መሆኑ ነው የገለጹት።
ምሑራኑ እንደሚሉት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተጀመረው “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በርካታ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቢቀጥል የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት፣ ለዜጎች የሥራ ዕድልን በመፍጠር እና አዳዲስ ቴክኖሎጂን ከማምጣት አንጻር ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል። ሀገርም የዕድገት ግስጋሴዋ ዘላቂና አስተማማኝ ይሆናል። የሥራ አጥነትም ችግርም በሂደት እየተፈታ ይሄዳል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2017 ዓ.ም