አሁን ፕሮፖዛል (የታገቢኛለሽ ጥያቄ) ይሉት ነገር በከተሞች ባሕላችን እየሆነ ነው። በፍቅረኝነት የከረሙ ጥንዶች ወንዱ ዘላቂ የትዳር አጋሩና ውሃ አጣጩ እንደምትሆን ሲወስን፤ እንዴት በሚያስገርም መልኩ ጥያቄዬን ላቅርብላት ሲል ይዘጋጃል። ያኔ ታዲያ ጌጣጌጥ(ዲኮር) ተስተካክሎ በደስታችን ተካፋይ መሆን ይገባቸዋል የሚላቸውን ሰዎች ጠርቶ፣ እንዴት ተምበርክኮ ታገቢኛለሽ ወይ እንደሚል ይለማመዳል። ታዲያ በመሰል ዝግጅቶች ጠሪ አክባሪ ብሎ ያለውን ልብስ ለብሶ መገኘት በቂ አልሆን እያለ ነው። ለነገሩ ልብስን ማስተካከል የሚጠይቀው የታገቢኛለሽ ጥያቄ ማቅረቢያ ግብዣዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ቤቢ ሻወር፣ ገአት (የአጥር ወፍ አትስማሽ) ዓይነት ለነብሰ ጡር የሚዘጋጁ የማስደሰቻ ዝግጅቶች አሉ። ከህጻን እስከ አዋቂ ያሉ የልደት ግብዣዎች፣ ሰርግ፣ ምርቃት፣ የድርጅት ዝግጅቶች ሽክ ማለትን ከሚሹ ቦታዎች የተወሰኑት ናቸው።
ዘመኑ ሲዘምን ሰዎች እንደ ዝግጅቱ ሁኔታ እንደ ሰዓቱ መልበስ ምርጫቸው እየሆነ ነው። ታዲያ በመሰል ዝግጅቶች ላይ የሚለበሱት አልባሳት ከአዘቦት ልብሶች ወጣ ያሉ ናቸው። ታዲያ ይሄኔ የኪራይ ልብስ ይሉት ነገር እዚህ ላይ ይመጣል።
በከተማችን ለመሰል ዝግጅቶች የሚሆኑ አልባሳትን ከበርካታ አማራጮች ጋር ከሚይዙ ቦታዎች አንዱ ርብቃ ህንጻ የሚገኘው ‹‹ዞዊ ፒክቸርስ ኤንድ ብራይዳል›› አንዱ ነው። የድርጅቱ ባለቤት ወይዘሮ ፍሬሕይወት አስራት ከዚህ ቀደም በሀገራችን ኪራይ በብዛት የተለመደው ለሰርግ ነበር ትላለች። የሙሹሮች አልባሳት፣ የሚዜ የአጃቢና አልፎ አልፎ ሰርግ ላይ የሚታደሙ ለየት ያለ ልብስ መልበስ ሲፈልጉ መከራየት የተለመደ ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዲት ሴት ለማግባት ስታስብ ጓደኞቿ ብራይዳል ፓርቲ ያዘጋጁላታል። ብራይዳል ሲያዘጋጁ ጓደኞቿ በብዛት ለሙሽራዋ እንደ አስፈላጊነቱ ለራሳቸውም የሚያጅቡበት ልብስ ተከራይተው ሰፕራይዝ ያደርጓታል። በተመሳሳይ የታገቢኛለሽ ድግሶች ራሱ ከሠርግ ያልተናነሱ ሆነዋል። በዚህ ዝግጅት ላይ ታዲያ የምትታጨው ልጅ አትወቅ እንጂ ወንዱ ፍቅረኛዬን ለጋብቻ ልጠይቅ ነው የሚላቸው በብዛት ሰምተው ለፕሮግራሙ ይሆናል ብለው የሚያስቡትን ልብስ አዘጋጅተው ይገኛሉ። ዝግጅቱ ከፍ ያለ ከሆነ ደግሞ የሚለብሱት ልብስ ምን መሆን እንዳለበት (ድሬሲንግ ኮድ) ይነገራቸዋል። ታዲያ የመድረኩ ንግሥት የምትሆነው ሴት ስለዝግጅቱ ስለማታውቅ በአብዛኛው ዝግጅቱ ላይ በአዘቦት ልብሷ ትገኛለች። ዘመነኛው ዝግጅት ከሰርግ አይተናነስምና በዝግጅቱ ላይ ቪዲዮና ፎቶ አለ። በእለቱ የታገቢኛለሽ ጥያቄ የሚቀርብላት የወደፊት ሙሽራ ከታዳሚው ጎልታ እንድትታይ ይፈለጋል።
እንደ ወይዘሮ ፍሬሕይወት ማብራሪያ፤ በብዛት ጥያቄው የሚቀርብላት ሴት የሚደረገውን ነገር ስለማታውቅ ፍቅረኛዋ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን በኦንላይን ያሉት አማራጮችን በማየትና በስልክ በማናገር ይከራያሉ ትላለች። አንዳንዴ በአካል በመምጣት ከሴቷ ጋር ተቀራራቢ ተክለሰውነት ያላት ጓደኛዋ ልብሶቹን በመለካት የተሻለ ሊያምርባት የሚችለውን ልብስ ይመርጣሉ። እነዚህ ልብሶች ታዲያ ጥያቄው የሚቀርብላትን ሴት ከሌሎች ታዳሚዎች እንድትጎላ የሚያደርጉ ስለሆነ ዋጋቸው ውድ ነው። ግለሰቦች የመግዛት አቅም ቢኖራቸው እንኳን ልብሶቹ ለየት ያሉና የተወሰነ ቦታዎች ብቻ ሊለበሱ የሚችሉ በመሆናቸው ከመግዛት ይልቅ በርካቶች መከራየት ምርጫቸው ነው። የተጠያቂዋ ጓደኞችም ተመሳሳይ ልብስ የሚከራዩበት አጋጣሚ መኖሩን ትናገራለች።
ሌላው በርካታ ሰዎች ዘመናዊ ልብሶችን ለኪራይ የሚፈልጉበት አጋጣሚ ምርቃት ነው። በፊት ከዩኒቨርሲቲና ከኮሌጅ ትምህርት ሲጨርሱ የነበረው ምርቃት አሁን ወደ 12ኛ ክፍል ማጠናቀቅ ዝቅ ብሏል። ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ መውሰዳቸውን በማስመልከት በየትምህርት ቤቱ የምርቃት ዝግጅት ያዘጋጃሉ። ያኔ በቡድንም ሆነ ከወላጆች ጋር እየመጡ ካሉት ልብሶች መካከል ይከራያሉ። ‹‹ለፕሮግራም የሚሆኑ ልብሶች ዋጋቸው ውድ ነው›› የምትለው ፍሬሕይወት፤ ሰዎች ፕሮግራሙ ተቃርቦ ለመግዛት ገበያ ወጥተው የሚፈልጉትን አማራጭ ገበያ ላይ አያገኙም ትላለች። በዚህ የተነሳም ለፕሮግራማቸው ከእነሱ መከራየትን አማራጭ ይወስዳሉ።
‹‹ወንዶች እንደ ሴቶች ብዙ አይከራዩም›› የምትለው ወይዘሮ ፍሬሕይወት፤ ወንዶች የሙሽራ፣ የሚዜ፣ እና የምርቃት እንደሚከራዩ ታነሳለች። በተለይ ተመራቂ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ከ12 ሺ እስከ 20 ሺህ ብር ወጪ አውጥተው ሱፍ ከመግዛት ስለዳኑ ደስተኛ መሆናቸውን ትናገራለች። የወንዶች ሱፍ አነስተኛ የኪራይ ዋጋ 500 ብር ነው የምትለው ወይዘሮ ፍሬሕይወት፤ እንደ ሱፉ ዓይነት እስከ 3000 ሺህ ብር የሚከራያ ዋጋ የተቆረጠላቸው የወንድ ሱፎች እንዳላቸውም ታስረዳለች። ታዲያ ተመራቂው ብቻ ሳይሆን በምርቃት ዝግጅቱ ላይ የሚታደሙ ቤተሰቦችና ጓደኞችም የሚከራዩበት ሁኔታ አለ። በተለይ ከኮሌጅና ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ተማሪ ወላጆች የኪራይ አማራጭ መኖሩን ሲያዩ ደስተኛ እንደሚሆኑና በተደጋጋሚ “ገላገላችሁኝ” እንደሚሏቸው ታስታውሳለች።
ወደሥራው እንደገባች መጀመሪያ አካባቢ በርካታ ሰዎች የሰው ልብስ ያመኛልና መሰል አስተያየቶች ይሰጧት እንደነበር የምታስታውሰው ወይዘሮ ፍሬሕይወት፤ አሁን እነሱም የደምበኞችን ምቾት ከመጠበቅ አንጻር ልብሶች ሲመለሱ ወዲያው እያጠቡና እየተኮሱ እንደሚያዘጋጁ ታስረዳለች። የኪራይ ልብስ እየተለመደ ስለመጣ የሚከራዩትም ሰዎች መልበስን እየተለማመዱት መሆኑን ትጠቅሳለች። ሳይዝ ለአብዛኛው ሰው እንዲበቃ በማለት ተለቅ ያሉ ልብሶችን ነው የምናስመጣው የምትለው ወይዘሮ ፍሬሕይወት፤ የምትከራየው ተከራይ ተለክታ በመጠኗ (ሳይዟ) እንዲጠብላት ይደረጋል። አነስ ያለ መጠን (ሳይዝ) ልብስ ካስገባን ለቀጭን ሰው ብቻ ስለሚሆን በተቻለ አቅም ለሁሉም ግልጋሎት ለመስጠት ከፍ ያለ ሳይዞችን ይይዛሉ። የሚዜ ልብሶች ግን ሙሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ሳይዞች እንይዛለን ትላለች። ለዝግጅት የሚሆኑ ልብሶች ይለያሉ። ሰዎች ሌላ ፕሮግራም ላይ የለበሱትን ልብስ ደግሞ መልበስ ምርጫቸው አይደለም። በዚህ የተነሳ አንዴ ተለብሶ ከሚቀመጥ ከዋጋም አንጻር ለዝግጅት የኪራይ ልብስ የብዙዎች ምርጫ እየሆነ ነው።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም