ሀገሪቱ ምግብ በበቂ ሁኔታ አሰባጥሮ ባለመመገብ ከአስራ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ ገቢ ታጣለች

አዲስ አበባ፡- ምግብ በበቂ ሁኔታ በአግባቡ አሰባጥሮ ባለመመገብ ምክንያት ሀገራችን ከአስራ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ ገቢ እያጣች መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ ።በሀገራችን ከሚከሰተው የህጻናት ሞት ሶስት አራተኛው በአመጋገብ ችግር እንደሆነ ተጠቆመ ።

በጤና ሚኒስቴር የሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ እና የማህበረሰብ ባህሪ ለውጥ ተግባቦት አማካሪ ቤዛዊት ታምሩ እንዳስታወቁት ፤ በበቂ ሁኔታ ምግብን በአግባቡ አሰባጥሮ በመመገብ ጤንነትን መጠበቅ ይቻላል፡፡

በሀገራችን ከሚከሰተው የህጻናት ሞት ሶስት አራተኛው ከተመጣጠነ የአመጋብ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የሚከሰት እንደሆነ ያመለከቱት ሃላፊዋ ፣ ዕድሜያቸው ከአስር ዓመት በታች የሆኑ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ህጻናት በአመጋገብ ችግር ምክንያት የመቀጨጭ ችግር አለባቸው ብለዋል።

67 በመቶ አምራች የሚባለው ማህበረሰብም በመቀንጨር ሂደት ያለፈ መሆኑን አመልክተው ፣ ከአመጋገብ ችግር ጋር ተያይዞ በሚፈጠር የጤና ችግር ሀገራችን ከአስራ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ ገቢ እያጣች መሆኑንም አስታውቀዋል ፡፡

የሥርዓተ ምግብ አለመመጣጠን ለተለያየ በሽታ የሚዳርግ ነው ፤ መቀንጨር፣ ከክብደት በታች መሆን እንዲሁም ለሰውነታችን አስፈላጊ የሆኑ ጥቃቅን ንጥረ ነገሮች ፤ ቫይታሚን ሲ፣ ዲ፣ እና ኢ የመሳሰሉት እጥረት ለደም ማነስ ፣ ለሪኬት እና ለጎይተር ለመሳሰሉ በሽታዎች ያጋልጣል ብለዋል፡፡

መቀንጨር ሲባል አንድ ልጅ በዕድሜው የሚታየው ቁመት ማነስ ብቻ ሳይሆን የአእምሮ እድገት ፣ የትምህርት አቀባበልን ጨምሮ ማህበራዊ ግንኙነትን ችግር ውስጥ የሚከት እንደሆነ የጠቆሙት ሃላፊዋ ፣ ነገሮችን በመወሰን እና በማሰብ ችሎታ ላይ ችግር የሚያስከትል የሀገር እና የማህበረሰብ ጠንቅ እንደሆነ አመልክተዋል ፡፡

በተለይ ነብሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ለሰውነታቸው እጅግ ጠቃሚ የሆነ አይረን እና ፎሊክ አሲድ ያስፈልጋቸዋል ፤ ወጣቶች እና አፍላ ወጣቶችም ለአይረን እጥረት የተጋለጡ ናቸው፤ ይህም ለደም ማነስ በተለይ አሁን ላይ በሀገራችን እየተስተዋለ ላለው የህፃናት የአፈጣጠር ችግር ያጋልጣል ብለዋል ፡፡

በተለይ በአዋቂዎች ላይ የሚስተዋለው የምግብ እጥረት ብቻ ሳይሆን ከመጠን በላይ መመገብ ፣ የታሸገ ምግብ እና ብዙ ጣፋጭ በመመገብ ምክንያት የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ ፣ የደም ግፊት እና የስኳር የጤና በሽታዎች በስፋት እየተስተዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።

የፎሊክ ምግቦች የሚባሉ አረንጓዴ ቅጠሎች፣ ምስር እና የእንስሳት ተዋፅኦ በመመገብ በሽታዎች መከላከል ይቻላል ፤ ማህበረሰቡ የተለያየ ይዘት ያለው የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እንዲችል የሌማት ትሩፋት እና የመሳሰሉ መርሃ ግብሮች ሊበራከቱ ይገባል ብለዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You