የአዲስ አበባ፦ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ 112 ተሽከርካሪዎች እና 1 ሺ 346 ምድብ ንብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ 74 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ለከተማ አስተዳደሩ ገቢ ማድረጉን አስታወቀ። በንብረቶች አወጋገድ ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት መኖሩን ጠቆመ ።
የአገልግሎቱ የንብረት ዋጋ ግመታ እና ማስወገድ ዳይሬክቶሬት የአምስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በቀረበበት ወቅት ፤ የዳይሬክቶሬቱ የንብረት ርክክብና ክትትል ቡድን መሪ አቶ ኃይለመስቀል አሰፋ ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች በሽያጭ እንዲወገዱ ውሳኔ የተሰጠባቸውን ንብረቶችን ለማስወገድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል ።
የአገልግሎት ዘመናቸውን ያጠናቀቁ እና ያለጥቅም ተከማችተው የሚገኙ ንብረቶችን እንዲወገዱ ለማድረግ ከተለያዩ የዘርፍ መሥርያ ቤቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ጥረት መደረጉን አመልክተው ፤ የንብረት አወጋገድ ጥያቄ ለማቅረብ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን በተገቢው መልኩ አደራጅተው እንዲያቀርቡ ሰፊ ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል ።
‹‹በሽያጭ እንዲወገዱ ውሳኔ የተሰጠባቸው 710 ምድብ ንብረቶች ናቸው›› ያሉት ቡድን መሪው፤ ንብረቶቹን በሽያጭ ከማስወገዱ አስቀድሞ የ35 ተሽከርካሪዎችን መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ስለመከናወኑም አውስተዋል።ለእነዚሁ 35 ተሽከርካሪዎች የጨረታ መነሻ ዋጋ ለማዘጋጀት ታቅዶ ሲሠራ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
አንድ ሺህ 346 ምድብ ንብረቶችና 112 ተሽከርካሪዎች መረጃ በማጣራት የተሽከርካሪዎቹን የምድብ ንብረቶቹም አፈፃፀም መቶ ከመቶ በላይ መሳካቱንም አመልክተው ፣ አፈጻጸሙ ከፍ እንዲል ካደረጉት ምክንያቶች አንዱም ‹‹በወቅቱ የሸገር ዳቦ ባስ መሸጫ የነበሩ አውቶቡሶች እንዲወገዱ መደረጉ ነው›› ብለዋል፡፡
የባቡር ሃዲድን ጨምሮ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች ፣ ባዶ የቶነር ካርትሬጅ እና ተጠግነው አገልግሎት መስጠት የማይችሉ ኮምፒውተርና ተያያዥነት ያላቸው የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ርክክብ መደረጉን አስታውቀዋል
ንብረት የሚወገድላቸው ተቋማት አስፈላጊውን መረጃ አደራጅተው አለመላክ፣ በየተቋማት የሚገኙ ባለሙያዎችም ሆነ አመራሮች በቂ ግንዛቤ ያላቸው አለመሆኑ፤ የሚወገዱ ንብረቶችን ለተጫራቾች በአግባቡ አለማሳየት ካጋጠሙ ችግሮች በዋነኝነት ተጠቃሽ መሆናቸው አመልክተዋል፡፡
ችግሮቹንም ለመፍታት የሚወገዱ ንብረቶች መረጃ መሰብሰቢያ ቅጽ አዘጋጅቶ መላክን ጨምሮ ፤ በመረጃ አደረጃጀት ላይ ድጋፍና ክትትል ተደርጓል ፣ በተቋማት በመገኘት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች እንዲሠሩ መደረጉንም ገልፀዋል።
በቀጣይም የተከማቹ ንብረቶችን መረጃቸውን አደራጅቶ በሽያጭ በማስወገድ ተጨማሪ ገቢን ለከተማ አስተዳደሩ ማስገባት፣ የባለሙዎች አቅም መገንባት እና በከተማ አስተዳደር ስር ለሚገኙት የተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠትን የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆን አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በሕግ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት አንዱ ያለ አገልግሎት የተቀመጡ ንብረቶች እንዲወገዱ ማድረግ ነው።ይሄን መሠረት በማድረግም አገልግሎቱ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ አገልግሎት የማይሰጡና ያለ አገልግሎት የተቀመጡ ንብረቶችና ግብዓቶች ክምችት ሕጋዊ ሥርዓት ተበጀቶላቸው እንዲወገዱ እያደረገ ይገኛል፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም