አዲስ አበባ፡- የባቱ ከተማ የቱሪዝም አቅም ለማሳደግ በ16 ሚሊዮን ብር የወርጃ ተራራ እና የአርዳ ጅላ ፕሮጀክቶች ሥራ መጀመሩን የከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።ፕሮጀክቶቹ የባህል አዳራሽ፣ ሐውልቶች፣ ቤተ መጻህፍት፣ መንገድ፣ ሰው ሠራሽ ሐይቅ፣ የተለያዩ መናፈሻዎች፣ ከ16 በላይ የቱሪስት ማደሪያ ቤቶች እና ሪዞርት የያዙ መሆናቸውን ገለጸ።
የባቱ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ከማል በዳሶ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ የከተማውን የቱሪዝም አቅም እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋን ለማሳደግ በ16 ሚሊዮን ብር የወርጃ ተራራና የአርዳ ጅላ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀምሯል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የአካባቢው ማህበረሰብ ባህል ለማጠናከርና የተረሱ ባህሎች ዳግም እንዲያንሰራሩ ለማድረግ እንደሚደረጉ አስታውቀው ፤ አርዳ ጅላ በኦሮሞ ሕዝብ ባህል የሚታወቅና የገዳ ሥርዓት ላይ ዋና ዋና የባህል ክዋኔዎች የሚከወኑበት ቦታ መሆኑንም ገልጸዋል።ሕግ የሚወጣበት፣ ተፈጻሚ የሚደረግበት፣ የሥራ አስፈጻሚዎች የሚሾሙበት፣ የገዳ ሥርዓት የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበትና ሥራው የሚገመገምበት ነው ብለዋል ። በቦታው ከጥንት ጀምሮ የነበረ ከሁለት ሺህ ሰዎች በላይ የሚይዝ ዋርካ መኖሩን ጠቁመዋል።
ባቱ ከተማ በተፈጥሮ የራሷ ለቱሪስት መስህብ የሚሆኑ አምስት ደሴቶች፣ ገዳማትና አድባራት፣ ከ270 በላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸው አእዋፋት እንዲሁም የጉማሬ መንጋ ያላት ከተማ ናት ያሉት አቶ ከማል፤ በከተማው የሚገኙ ሐይቆች ዙሪያን የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።ቦታው የቀድሞ የኦሮሞ አባቶች የገዳ ሥርዓት ሲከውኑበት ቢቆዩም በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለመንግሥት አገልግሎት ውሎ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ ፕሮጀክቶቹ የባህል አዳራሽ፣ የኦሮሞ ባህል የሚያሳዩ ሐውልቶች፣ ቤተ መጻህፍት፣ መንገድ፣ ሰው ሰራሽ ሐይቅ፣ የተለያዩ መናፈሻዎች፣ ከ16 በላይ የቱሪስት ማደሪያዎች ቤቶች፣ ሪዞልት የያዙ ናቸው። ለኪነ ጥበብና መዝናኛ የሚሆኑ ሥፍራዎች፣ በገዳ ሥርዓት መሠረት ለአባ ገዳ፣ አደ ሲንቄና ለወጣቶች መቀመጫ ቦታዎች ተካተውበታል፡፡
ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከከተማቷ ነዋሪዎች እስካሁን 300 ሺህ ብር ተሰብስቧል ፤ ፕሮጀክቱ እስከ ግንቦት ድረስ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ለከተማው ቱሪዝም እንቅስቃሴ እና ለኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽጾ እንደሚኖራቸው አስታውቀዋል። በተለይ አርዳ ጅላ ሲጠናቀቅ እስከ ስምንት ሺህ ሰው ድረስ ማስተናገድ የሚችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በከተማው በተያዘው ሩብ ዓመት ብቻ የሀገር ውስጥ ቱሪስት ሳይጨምር 388 የውጭ ቱሪስቶች በማስተናገድ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ተገኝቷል ያሉት አቶ ከማል፤ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ዘጠኝ ሚሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም