ዜና ትንታኔ
መንግሥት በምእራብ ሸዋ ትጥቅ አንግቦ ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ከሰሞኑ የሰላም ስምምነት መፈራረሙ ተገልጿል። ይህንኑ የሰላም ስምምነት ተከትሎም የታጣቂ ቡድኑ አባላት በብዛት ወደተሀድሶ ማእከላት እየገቡ መሆኑ ተነግሯል።
ለመሆኑ በመንግሥትና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት አንድምታ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መነፅር እንዴት ይታያል? አሁንም ድረስ በትጥቅ ትግል እየተንቀሳቀሱ ላሉ ቡድኖችስ ምን መልእክት ያስተላልፋሉ?
አቶ ካህሳይ ዘገየ የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ናቸው። እንደርሳቸው ገለፃ፤ በመንግሥትና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት በበጎ የሚታይ ነው። በተለይ ስምምነቱ ጦርነት ቀርቶ ሁሉም ነገር በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይትና በድርድር ማለቅ አለበት በሚል የተከናወነ መሆኑ እንደ መልካም ጅምር የሚታይ ነው። ጅምሩ በሌሎች አካባቢዎች የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ በውስጥ ለሚገኑ ሃይሎች መልካም ተሞክሮ ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነ ይናገራሉ።
የተደረገው የሰላም ስምምነት በጦርነት የሚገኝ አንድም ትርፍ እንደሌለ የሚያሳይም ጭምር መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ካህሳይ፤ ጦርነት አውዳሚና ልማት አጥፊ በመሆኑ ሁሌም ቢሆን ሰላም ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ። ጦርነት የሀገር ኢኮኖሚንና ልማትን ወደኋላ የሚጎትት ከመሆኑ ባሻገር በንፁሃን ላይ የሚያስከትለው እልቂት፣ መፈናቀልና ስደት ቀላል የሚባል አይደለም ፤ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች ይህንን በአግባቡ ተረድተው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከመንግሥት ጋር መስማማታቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።
ሌሎች የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖችም ይህንኑ የሰላም መንገድ ሊከተሉ እንደሚችሉ ያላቸውን ግምት ያስቀምጣሉ። የተደረገው የሰላም ስምምነት በቀላሉ እንደማይታይም አቶ ካህሳይ ገልፀዋል፤ መንግሥት ለታጣቂ ቡድኖች በተደጋጋሚ ያቀረበው የሰላም ጥሪና ህብረተሰቡም ሰላም እንዲመጣ ያደረገው ተማፅኖ ምላሽ እንዳገኘ ማሳያ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህም ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ አርአያ የሚሆን ተግባር ነው ይላሉ።
የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አውግቸው ማለደ በበኩላቸው ፤አቶ ካህሳይ ባነሱት ሃሳብ በመስማማት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስኖ ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሙ ተገቢና የሚደገፍ ተግባር መሆኑን ይገልፃሉ። በፖለቲካ ትግል ከትጥቅ ጀምሮ ሁሉም አይነት የትግል አማራጮች እንዳሉ ጠቅሰው፤ እነዚህ የትግል አማራጮች ለውጥ ከመፈለግ የመነጩ መሆናቸውን ያስረዳሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ሰላማዊ የትግል መስመርን መከተል አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አፅንኦት ይሰጣሉ።
ለውጥ እናመጣለን ወይም የመንግሥት ሥርዓት አልተመቸንም በሚል ጫካ የገቡ ኃይሎች የሰላማዊ ትግል ስልትን አማራጭ አድርገውና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ያለምንም ጦርነትና መስዋትነት ብሎም ሰላማዊ ዜጎችን አደጋ ውስጥ በማይጥል መንገድ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መወሰናቸው በጥሩ የሚታይ ተግባር መሆኑን ነው። ለዚህ ደግሞ በተለይ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የወሰደው የሰላም ርምጃ የትጥቅ ትግልን እንደአማራጭ ወስደው እየተንቀሳቀሱ ላሉ ሌሎች ቡድኖች አርአያ የሚሆን ተግባር እንደሆነም አቶ አውግቸው ያመለክታሉ።
ከዚህ በፊት በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረገው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እንደ ትልቅ የመዓዘን ድንጋይ መታየት አለበት። የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሰላም እንጂ ጦርነት የቱንም ያህል አዋጭ እንዳልሆነ ጥሩ ማሳያ ነው።ስምምነቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነት አውዳሚ መሆኑን በመረዳት የእርስ በርስ ግጭቶችንና አለመስማማቶችን በውይይትና በሰላም መቋጨት እንዳለባቸው አመላካች መሆኑንም አቶ ካህሳይ ተናግረው፤ በተመሳሳይ አሁን የተደረሰው የሰላም ስምምነትም የዚሁ አንዱ ማሳያ መሆኑን ይጠቁማሉ።
አቶ አውግቸው ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት በመንግሥት በኩል የተለያዩ የሰላም ጥሪዎች መደረጋቸውን አስታውሰው፤ ጫካ በገቡ ሃይሎች በኩል መንግሥትን የመጠራጠር ሁኔታዎች እንደነበሩ ያስረዳሉ። ችግሩ ታጣቂ ሃይሎች ወደሰላማዊ ድርድር ሲመጡና ከመጡም በኋላ እንቅፋት ሊፈጥር ስለሚችል ለጉዳዮ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ አቶ አውግቸው ይገልጻሉ።
የአረና ትግራይ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ካህሳይ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን በመንግሥትና በታጣቂ ኃይሎች መካከል የሚደረገውና እየተደረገ ያለው የሰላም ስምምነት ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ በርካታ የሰው ሃይል በተለይም ወጣቱ ከሞት እንደሚተርፍ፣ የሀብትና ንብረት ውድመት እንደማይኖር፣ አስተማማኝ ፀጥታና ሰላም በሀሪቱ እንደሚሰፍንና የሚጠበቀው ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚሳካ ያላቸውን ተስፋ አመላክተዋል።
የሰላም ስምምነት ቸል የሚባል ከሆነና ታጣቂ ቡድኖችም የሰላም አማራጭን ወደ ጎን ትተው በትጥቅ ትግል መንገድ የሚቀጥሉ ከሆነ በሀገሪቱ የሰው እልቂት፣ የሀብትና ንብረት ውድመት፣ ስደት፣ መፈናቀልና የኢኮኖሚ ድቀት የሚከሰት እንደሆነ ነው ያላቸውን ስጋት የሚገልፁት።
የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አውግቸው በበኩላቸው፤ በአቶ ካህሳይ ሃሳብ በመስማማት ከዚህ በፊትና አሁን ላይ በመንግሥትና በታጣቂ ኃይሎች መካከል የሚደረገውና እየተደረገ ያለው የሰላም ስምምነት ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ከማድረጉም በላይ በመሣሪያ ከመዋጋት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ ልዩነትን በሃሳብ የመፍታት ባህል እንዲዳብር የሚያስችል መሆኑን ይጠቁማሉ።
ሁለቱም ፖለቲከኞች የሚስማሙት የሰላም ስምምነት ለማንም ለምንም ወሳኝና ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ነው። አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር ሊፈቱ ፤ ማንኛውም ትጥቅ ትግል የሚያካሂድ ቡድን የሰላም ስምምነትን ቅድሚያ ሊሰጥና ሊቀበል ይገባል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም