አዲስ አበባ፡- ከሰሞኑ እየተስተዋለ ያለው ቀዝቃዛማ አየር እስከ ታህሳስ 12 ስለሚቀጥል ከአየር ጠባዩ ጋር የሚስማማ አለባሰበስ ሊኖር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትንበያና ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ኢንስቲትዩቱ የአየር ሁኔታ መረጃዎች በመሰብሰብ ትንበያዎችንና ምክረ ሃሳቦችን በማዘጋጀት፤ በአየር ጠባይ መለወጥና መዋዠቅ ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በመሥራት መረጃዎንችን ለሕዝብና ለሚመለከታቸው ተቋማት ያደርሳል።
እንደ ሀገር ክረምት በጋና በልግ የሚባሉ አራት፤ አራት ወራት ያሏቸው ሶስት ወቅቶች መኖራቸውን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ወቅቶቹን መሠረት በማድረግ በእያንዳንዱ ወቅት ስለሚኖረው የአየር ጠባይ አዝማሚያ ኢንስቲትዩቱ አስቀድሞ የተለያዩ የአየር ሁኔታ ክስተቶችን ዋቢ በማድረግ በዓመት ሶስት ጊዜ የትንበያ መድረኮች ያዘጋጃል።
እንደ አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ገለጻ ፣ ባለፈው ነሀሴ ወር 2016ዓ.ም በዘንድሮው በጋ 2017 ዓ.ም ምን አይነት የአየር ጠባይ አዝማሚያ ሊስተዋል እንደሚችል ትንበያ እና ምክረ ሃሳብ በማዘጋጀት ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተደራሽ እንዲሆን አድርጓል ፡፡
በጋ የሚባለው ከጥቅምት እስከ ጥር ያሉት ወራቶች መሆናቸውን የጠቆሙት አሳምነው (ዶ/ር) ፤ በተለይም ለደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍልና አካባቢ ማለትም ለሶማሌ ደቡባዊ ክፍል፤ ለጉጂ ዞኖች፤ ቦረና ዞኖች፤ ለሲዳማና ለደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ሲሆን ከዓመታዊ የዝናብ መጠኑ 45 በመቶ የሚደርስ የዝናብ መጠንና ስርጭት ይስተዋልባቸዋል።
በበጋ ወቅት ደረቅ፤ ፀሀያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚስተዋልበት ወቅት መሆኑን ያስታወሱት አሳምነው (ዶ/ር)፤ በዚህ ወቅት ከሳይቤሪያ በመነሳት ወደ ሀገሪቱ የሚገባው ደረቅና ቀዝቃዛማው የአየር ሁኔታ የሚጠናከርበት ነው።ይህም ወደ ሀገሪቱ የሚገባው የአየር ሁኔታ ከባለፉት አምስት ቀናት በተወሰኑ የምስራቅ አማራ አካባቢዎች፤ በመካለኛው እና በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የለሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ እንዲጠናከር አድርጓል።
ከዚህ ቀደም ቅዝቃዜ ሊስተዋል የሚችለው ጥቅምት እና ህዳር ወር ላይ ነበር፤ በዘንድሮው ዓመት ግን በእነዚህ ሁለት ወራቶች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስለነበር ከህዳር ወር መጀመሩን አመልክተው ፣ አሁን ላይ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የደመና ክምችት ስለማይስተዋል የለሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ለዚህም በዋናነት ከሳይቤሪያ ላይ በመነሳት ወደ ሀገራችን የሚገባው ደረቅና ቀዝቃዛማው የአየር ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት ከመጠናከሩ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። በመሆኑም በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሙቀት መጠኑ ከአምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በታች የተመዘገበባቸው ሁኔታዎች አሉ።
ለአብነትም በደባርቅ፤ አምባ ማሪያም፤ ሾላ ገበያ፤ ደብረ ብርሃን፤ በባቲና መሰል አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ ከአምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በታች የሆነ የማለዳው ቅዝቃዜና የሙቀት መጠን እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ አድርጓል። በአንዳንድ አካባቢዎችም ከዜሮ በታች እስከ ነጋቲቭ አንድ ነጥብ ስድስ ድረስ የተመዘገበ የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
የአሁኑ ወቅት የቅዝቃዜ መጠን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ማለትም ከህዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 ድረስ ያለውን መረጃ ጋር ሲነጻጸር በአዲስ አበባ ከተማና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የቅዝቃዜው መጠን ጨምሯል።ዋና ምክንያቱ ከሳይቤሪያ የሚነሳው ነፋስ ይበልጥ ከዕለት ወደ እለት በመጠናከሩ ነው። ይህም እስከ ቀጣዩ ታህሳስ 12 ቀጣይነት እንደሚኖረው የትንበያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ አሳምነው (ዶ/ር)ገልፀዋል።
እየተስተዋለ ያለው የበጋው ደረቅ ጸሃያማ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በተለይም በመኸር ወይም በክረምት ወቅት የተዘሩ ሰብሎችን በአግባቡ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ቅዝቃዜው እስከ ታህሳስ 12 ድረስ ቀጣይነት እንደሚኖረው ህብረተሰቡ ተገንዝቦ በዕየለቱ ምን አይነት የአየር ሁኔታ እንደሚስተዋል ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በዕየለቱ ከሚኖረው የአየር ጠባይ ጋር የሚስማማ አለባሰበስ ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም