ከኬንያ ወደ ታንዛኒያ የተዘረጋው የኃይል አቅርቦት ማስተላለፊያ መስመር የሙከራ ኃይል አቅርቦት ጀመረ

አዲስ አበባ ፦ የምስራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ ሃይዌይ (East Africa Electric Highway) ፕሮጀክት የኢትዮጵያ፣ የኬንያና የታንዛኒያ የኃይል መሠረተ ልማት አካል የሆነው ኃይል ከኬንያ ወደ ታንዛኒያ የሚያስተላልፈው መስመር የሙከራ የኃይል አቅርቦት ትናንት ጀምሯል።

የምስራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ ሀይዌይ ፕሮጀክት የመጀመሪያው የኃይል ትስስር በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ፤ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በተዘረጋው የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማት ተግባራዊ መሆኑ ይታወሳል ። የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ክፍል በኬንያ በኩል ወደ ታንዛኒያ የተዘረጋው የኃይል አቅርቦት ትስስር መስመር ነው፤ ይህ የኤሌክትሪክ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተጠናቆ ትናንት የሙከራ ኃይል አቅርቦት ጀምሯል።

ይህ ቀጣናዊ የኃይል ትስስር ኢትዮጵያ ያላትን የታዳሽ ኃይል አቅርቦት በማስፋፋት የአረንጓዴ የኤሌክትሪክ ኃይል ግብይትን በተመጣጣኝ ዋጋ በማረጋገጥ በሀገራት መካከል ትብብርን ያመጣል፤ ብልፅግናን ያሰፍናል ፣ኢትዮጵያ የኃይል ትስስር በቀጣናው እንዲስፋፋ ሚና እንድትጫወት ያስችላታል ተብሎ ይታመናል።

ኢትዮጵያ በመጀመሪያዎቹ የግብይት ዘመናት በዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ እንድታገኝም የሚረዳት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ፣ለፕሮጀክቱ የዓለም ባንክ ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና የፈረንሳይ የልማት ፋይናንስ ተቋም ድጋፍ ማድረጋቸውም ተመልክቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You