በኦሮሚያ ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ 8ሺህ የሚደርሱ ተወካዮች ይሳተፋሉ

አዳማ፡- በኦሮሚያ ክልል በሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ 8ሺህ የሚደርሱ ተወካዮች እንደሚሳተፉ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ። በክልሉ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክም ዛሬ እንደሚጀመር ተገለጸ።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ፤ በአዳማ ከተማ የሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 15 ለተከታታይ ቀናት የሚቆይ ነው።

በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኩ ከ7ሺህ በላይ የሚሆኑ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ከ356 ወረዳዎች የተመረጡ የማህበረሰብ ወኪሎች እና 1 ሺህ 700 የክልል ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል

ሂደቱን ከ350 በላይ ተባባሪ አካላት፣ 150 በጎ ፍቃደኞች እና 48 አስተባባሪዎች እንደሚያሳልጡ ያመለከቱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በአጠቃላይም 8ሺህ የሚደርሱ ተሳታፊዎች በመድረኩ እንደሚወከሉ አመላክተዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኩ አጀንዳዎች በውይይት እንደሚለዩ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ ፣ ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የኦሮሚያ ክልል ተወካዮችም እንደሚመረጡ ጠቁመዋል።

መድረኩ ሁለት ምዕራፎች እንዳለው የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ ፣ የመጀመሪያው ፣ ምዕራፍ ከ356 ወረዳዎች የተውጣጡ ከ7ሺ በላይ የህብረተሰብ ተወካዮች ለ 5 ቀናት ተወያይተው አጀንዳዎቻቸውን የሚለዩበት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚወያዩ ተወካዮቻቸውን የሚመርጡበት መሆኑን  ገልጸዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ፣ የተመረጡ የማህበረሰብ ወኪሎች ከአምስት ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ጋር እስከ ታህሳስ 15 የሚወያዩበት እና የክልሉን አጀንዳ አደራጅተው ለኮሚሽኑ የሚያስረክቡበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እስከ አሁን ካካሄዳቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮች የኦሮሚያው በተሳታፊ ቁጥር የላቀ መሆኑን ያመላከቱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ዛሬ የሚጀመረው መድረክ በርካታ ተሳታፊዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ ኮሚሽኑ ሰፊ ዝግጅት እንዳደረገበት አስታውቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት፣ የአዳማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት እና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ ሚዲያዎችም የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ሕዝብ ዘንድ በማድረስ እያበረከቱ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።።

ኮሚሽኑ እስከ አሁን በ9 ክልሎች እና በ2 ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ማጠናቀቁም በመግለጫው ወቅት ተገልጿል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You