የ “አይ ኤፍ ኤች” የዱላ ቅብብል ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ኢትዮጵያ የአትሌቶች መፍለቂያ መሆኗን ተከትሎ በየዓመቱ በርካታ የሩጫ ውድድሮች በተለያዩ የስፖርት ተቋማት አዘጋጅነት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች አስተባባሪነት ይከናወናሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነውና ረጅም ጊዜን ካስቆጠሩ ዓመታዊ የሩጫ ውድድሮች መካከል የሚጠቀሰው የአይኤፍኤች የዱላ ቅብብል ውድድር ነው።

አካልና አእምሮን ከማጎልበት ባለፈ በሰዎች መካከል መልካም ግንኙነትን የሚፈጥር በመሆኑ ከስፖርታዊ ተቋማት ውጪ በየትኛውም ዘርፍ መልዕክት ለማስተላለፍ እንዲሁም ለመዝናናት የሚመረጥ መሆኑ ይታወቃል። በኮንስትራክሽን ተቋማት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመሆን የሚደረገው ይህ ሩጫ ማሳያ ሲሆን፤ ዛሬ ለ19ኛ ጊዜ የሚከናወን ይሆናል።

ውድድሩ የአይኤፍኤች ኢንጂነሪንግ፣ ዘንድሮ 20ኛ ዓመቱን በኢትዮጵያ ያስቆጠረው የቻይናው የኮንስትራክሽን ድርጅት (CCCC) እንዲሁም የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዘርፍ የሚያከናውኑት ነው። ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስተባባሪነት የሚደረገው ሩጫውም በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው አዲሱ የቃሊቲ ቂሊንጦ መንገድ መነሻና መድረሻውን ያደርጋል፡፡

በአትሌቶች መካከል ከሚደረገው ሩጫ ባለፈ ሕዝባዊው ሩጫ የአዘጋጁን ተቋማት ሠራተኞች እንዲሁም የተለያዩ ኤምባሲዎችን እንዲሁም የመንግሥትና የግል ተቋማትን በማሳተፍ የሚደረግ መሆኑን የሩጫው አዘጋጅ ከሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሕዝባዊው የሩጫ ውድድር በርካታ ተሳታፊዎችን እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞችን በየአንድ ኪሎ ሜትሩ ዱላ በመቀባበል ይከናወናል። በአትሌቶች መካከል የሚካሄደው ውድድር ደግሞ በ የ3 ኪሎ ሜትሩ አትሌቶች እየተቀባበሉ 12 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሆኖ ይካሄዳል። በዚህም 50 የሚሆኑ ቡድኖች ለአሸናፊነት ይፎካከራሉ።

ዘንድሮ የተጀመረው ሌላኛው የሩጫ ዘርፍ ደግሞ የወጣቶች ዘርፍ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ርቀት እርስ በእርስ ፉክክር በማድረግ የውድድር ልምዳቸውን እንዲያሳድጉ ታሳቢ የተደረገ ነው። በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶችም የተዘጋጀላቸውን ሜዳሊያ እና የገንዘብ ሽልማት ይወስዳሉ፤ ይኸውም ቀዳሚ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ቡድን የ60 ሺህ፣ ተከታዩ የ40 ሺ እንዲሁም ሶስተኛው ቡድን የ25 ሺህ ብር ነው።

የዛሬውን የዱላ ቅብብል ሩጫ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ በመላው ዓለም 157 ሀገራት ላይ በተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የተሠማራው የቻይናው የኮንስትራክሽን ድርጅት (CCCC) በኢትዮጵያ 20ኛ ዓመት በማስቆጠሩም ነው። የብሄራዊ ስታዲየም ግንባታን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ የሆነው ተቋሙ የኢትዮጵያና ቻይና መልካም ግንኙነት ማሳያ ሊባል የሚችልም ነው። የሩጫ ውድድሩን ተከትሎ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሃመድ፤ ስፖርት ማህበራዊ መቀራረብን የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግሥት በስፖርት መሠረተ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ማሳያ ከሆኑት መካከል አንዱ በኮንስትራክሽን ተቋሙ(CCCC) እየተገነባ የሚገኘው ብሄራዊ ስታዲየም ነው። ከግንባታው ጎን ለጎንም ተቋሙ በስፖርት ተሳትፎ ማድረጉ የሚበረታታ እና ከቻይና ጋር ያለው የስፖርትና ባህል ግንኙነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራች የሆነው ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በበኩሉ፣ የኮንስትራክሽን ተቋሙ ከቴክኖሎጂ ሽግግር ባለፈ ጠንካራ የሥራ ባህልን ለኢትዮጵያውያን በማስተማራቸው ‹‹እናመሰግናለን›› ብሏል። ባለፉት 19 ዓመታት (ከመገናኛ እስከ ቃሊቲ የዘለቀውን የቀለበት መንገድ ግንባታ ተከትሎ) የተጀመረው ስፖርታዊ ውድድር ማዘጋጀት ዓመታትን በመዝለቅ ብዙዎችን የሚያገናኝ መድረክ መፍጠር ተችሏል። በቀጣይም ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር እንደሚሠሩም ጠቁሟል።

በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለሶስት ጊዜያት በመሳተፍ ሁለቱን በአሸናፊነት ያጠናቀቀችው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላውም ለሩጫው ተሳታፊዎች የመልካም ዕድል ምኞቷን አስተላልፋለች። በ10 ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት፣ በግማሽ ማራቶን ስኬታማና በማራቶን ውጤታማ እየሆነች የምትገኘው ኢትዮጵያ የዚህ ዓመት የአምስተርዳም ማራቶን አሸናፊ መሆኗ ይታወቃል። አትሌቷ መሰል ውድድሮች በሀገር ውስጥ በስፋት መካሄዳቸው በተለይ ለወጣት አትሌቶች የውድድር ዕድልን የሚያሰፋ በመሆኑ መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ነው የጠቆመችው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2017 ዓ.ም

Recommended For You