አዲስ አበባ፡- የኮሪደር ልማቶች የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ እድገት መሸከም የሚችሉና መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፣ የኮሪደር ልማቱ የነገውን እድገት መሸከም እንዲችል ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡
የመጀመሪያው ዙር ኮሪደር ልማት ዋና ዋና ሥራዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ለሕዝብ ክፍት መደረጋቸውን ያስታወሱት ከንቲባዋ፣ ለዋናው መንገድ መጋቢ የሚሆኑና 10 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 13 መንገዶች ተገንብተዋል ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ዓላማ መንገዶችን፣ ልማቶችን ማገናኘትና የትራፊክ ችግሩን መፍታት፣ ማሳለጥና ጽዳትን ማረጋገጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከቆሻሻና ካረጁ ነገሮች ጋር ከመኖር በመላቀቅ ውብና ጽዱ የሆነ አካባቢ መፍጠርና የሚያነቃቃ አካባቢን እንዲኖር ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመንገዶች ግንባታው ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴው፣ ለገቢ እድገትና ለሰዎች እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ዋና መንገዶችን ጨምሮ መጋቢ መንገዶቹ ለከተማው ነዋሪዎችና ለንግድ እንቅስቃሴዎች እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ልማቱ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት፣ የትራፊክ እንቅስቃሴን ለማሳለጥና ለሰዎች አማራጭ እግረኛ መንገድ እንዲያገኙ ያስችላል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ አንደኛው ዙር ኮሪደር ልማት የፒያሳና አካባቢውን ታሪክ መቀየር የሚችሉ ፣ በትልቅ ከፍታ ላይ የሚያስቀምጡ መሠረተ ልማቶች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ የመኪና ማቆሚያዎች፣ አውቶቢስና የታክሲ ተርሚናሎች፣ ፕላዛዎችና መጋቢ መንገዶች መሠራታቸውን ጠቅሰው፣ በመሬት ውስጥ የተሰሩ የውሃ፣ የፍሳሽ፣ የመብራት፣ የትራፊክ ማኔጅመንት፣ ሲሲ ቲቪ ካሜራ መሠረተ ልማቶችን ትልቅ ለውጥ ማምጣታቸውን አመላክተዋል፡፡
በልማቱ አቡነ ጴጥሮስ ፣ዳግማዊ ምኒልክ፣ ቴዎድሮስ አደባባይ፣ ሸዋ ሆቴል፣ ሜጋ አንፊ ቲያትር፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሀገር ፍቅር ቲያትር መታደሳቸውን ጠቅሰው፣ ነባሮችን በማደስ አዳዲሶችን ጨምሮ መሥራትን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮሪደር ልማት ለመጪው ትውልድ መሸጋገር እንዲችል ተደርጎ ተሠርቷል ያሉት ከንቲባዋ፣ አሁን የተሰሩ የኮሪደር ልማቶች ነገ የሚፈርሱ ሳይሆን መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡
ለኮሪደር ልማቱ ከሌሎች ሀገራት የተገኙ ልምዶች ሲተገበሩ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ታሳቢ አድርገው መሆኑን በመግለጽ፣ ዓላማው ታሪካችንን ለቱሪስቶች ማስጎብኘት ብቻ ሳይሆን መጪው ትውልድ የትናንትናውን ሳይረሳ ዛሬ የተሻለ ሕይወት እንዲኖር ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የተሠሩት መብራቶች፣ የደህንነት ካሜራዎች የከተማው ነዋሪዎች ደህንነት ተሰምቷቸው እንዲንቀሳቀሱ ማድረጉን ጠቅሰው፣ የኮሪደር ልማት የተሠራባቸው አካባቢዎች ላይ ቀደም ሲል ተቋማት ሲያስገቡ ከነበረው ገቢ 25 በመቶ እድገት ማሳየቱን አመላክተዋል፡፡
ልማቱ በኢኮኖሚ፣ በቱሪስት መስህብነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋት ገልጸው፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገባቸውን ክብር እንዲያገኙ ግብዓት እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም