በክልሉ አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በዘር ተሸፍኗል

አዲስ አበባ፡- በ2017 የበጋ መስኖ አራት ሚሊዮን ሄክታር ስንዴ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ድረስ አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ዘር መሸፈኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ የበጋ መስኖ ልማት የመስኖ ስንዴ ልማት እና መደበኛ የመስኖ ልማትን ያጠቃልላል፡፡ በ2017 የበጋ መስኖ ልማት አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት የበጋ መስኖ ለማልማት ታቅዷል፡፡ በመስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው አጠቃላይ መሬት ውስጥ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር የማሳ ዝግጅት ሥራ ተሠርቷል ያሉት አቶ በሪሶ፤ ከዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ደግሞ በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ 500 ሺህ ሄክታር መሬት በመደበኛ መስኖ ለመሸፈን መታቀዱን ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በአሁኑ ጊዜ የማሳ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ዘር መዝራት መገባቱን ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ያለው የሥራ አፈጻጸም ከተቀመጠው እቅድ አንጻር ጊዜው ጠብቆ እየሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ በየደረጃው ያለው አመራር ለአርሶ አደሩ የቅርብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የግብርና ሥራ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ እቅዱን ለማሳካት ከክልል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የልማት አጋሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች የሚያደርጉትን ርብርብ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የበጋ መስኖ ልማት አርሶ አደሩ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ እንዲያመርት በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You