በጋምቤላ ክልል እንደ ልብ መንቀሳቀስ የሚያስችል ሰላም መፍጠር ተችሏል

አዲስ አበባ፡‹‹በጋምቤላ ክልል እንደ ልብ መንቀሳቀስ የሚያስችል ሰላም መፍጠር ተችሏል›› ሲሉ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ አስታወቁ፡፡ በጋምቤላ ከተማ የኮሪደር ልማት ለማካሄድ ዲዛይን እየተዘጋጀ እንዲሁም የኦልዌሮ ግድብን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ርእሰ መስተዳድሯ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ ‹‹የሰላም እጦት በልማት ሥራዎች ላይ እንቅፋት ይፈጥራል፤ ቀደም ሲል ለተከታታይ ሁለትና ሶስት ዓመታት በክልሉ የእርስ በርስ ግጭት ነበር›› ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

ሰላምን ለማምጣት በተከናወነው ተግባር ባለፉት አራት ወራት የተፈጠረ የሰላም ችግር እንደሌለም ጠቅሰው፣ ህብረተሰቡ ለሰላም ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ሌላ ምንም ሳናደርግ ባደረግናቸው የጋራ መድረኮች ሰው እንደልቡ የሚንቀሳቀስበት እድል ተፈጥሯል›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህን ሰላም ዘላቂ የማድረጉ ሥራ ቀጣዩ የመጀመሪያ ሥራ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ያለ ሰላም ልማት አይኖርም፤ የልማት ፍላጎቱ ካለ ሰላም ሊኖር ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ የጀመርናቸው ጥሩ ጥሩ ሥራዎች አሉ ሲሉም አመልክተዋል፡፡

ክልሉን ወደኋላ የመለሰው የሰላም መናጋት ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሯ፣ ሰላም ለማምጣት ሰፊ ጊዜ ወስደን ሠርተናል፤ እንደሌሎች ክልሎች ልማቱን ለማስቀጠል የሚያስችል ሁኔታ እንደ ሰላሙ ሁሉ ክልሉ ከፈጠረ በእኛ አቅም የሚሠሩትን እኛ እንሠራለን፤ በፌዴራል ትኩረት ተሠጥቷቸው የሚሠሩ ካሉ ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ከአጎራባች ደቡብ ሱዳን ጋር ድንበር አካባቢ ከግጦሽና የመሳሰሉት ጋር በተያያዘ

የሚፈጠር ግጭት አለ፤ ህጻናትና ከብቶችን መውሰድም ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ የሙሩሌ ማህበረሰብ አባላትን በተመለከተ ከደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ጋር ሰሞኑን ውይይት ተደርጓል፡፡ ባለፈው ዓመትም መድረክ ተካሂዷል፤ ዘንድሮ በ2025 በደቡብ ሱዳን መድረክ የሚካሄድ ስለመሆኑ ከቀድሞው አመራር ጋር ስምምነት ተደርሷል ነው ያሉት፡፡

ድንበር አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች እንደሚመላለሱ ጠቅሰው፣ ‹‹ምንም የሚያጋጭ ነገር የለም፤ መሬቱ ሰፊ ነው፤ አብሮ መሥራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በእነሱ በኩል መመቻቸት ያለባቸው ነገሮች አሉ ሲሉም አመልክተዋል፡፡

ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መንገድ እየተገነባ መሆኑንም ርእሰ መስተዳድሯ ጠቅሰው፣ ያንን ግንባታ እኛም እነሱም ሃላፊነቱን ወሰድን እንዲለማ በማድረግ አካባቢውን ለልማት ማዘጋጀት ከሁላችን ይጠበቃል፤ እኛም በውጭ ጉዳይ በኩል በሚዘጋጁ የጋራ መድረኮች ላይ ትኩረት አድርገን እንሠራለን ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ርእሰ መስተዳድር አለሚቱ በጋምቤላ ከተማ የኮሪደር ልማት ለማካሄድ ዲዛይን እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ልማቱን በቀጣይም ወደ ወረዳዎች ለማውረድ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

በጋምቤላ ከተማ የኮሪደር ልማት በአጠቃላይ ወደ 22 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ጠቅሰው፤ በአራት ዋና ዋና መንገዶች ላይ ወደ 13 ኪሎ ሜትር የሚሆን ግንባታ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በቂ የተፈጥሮ ሀብት አለ፡፡ ፓርኩ፣ ወርቅና ቡና የክልሉ መገለጫዎች ናቸው፤ በቆሎ በስፋት ይለማል፤ ያጣነው ነገር የለም፤ የጋምቤላ ሰው ድርቅና የመሳሰሉት ቢከሰቱ በረሃብ አይሞትም፤ ምክንያቱ ሊጠቀማቸው የሚችሉ በርካታ ሀብቶች በአካባቢው ሞልተውታል፤ ይህን እምቅ ሀብት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ማስተዋወቅ ላይ ይሠራል፡፡

ርእሰ መስተዳድሯ ከደርግ ዘመን ተገንብቶ እስከ አሁን ብዙም ያልተሠራበትን የኦልዌሮ ግድብን ወደ ታለመለት ልማት ሙሉ ለሙሉ ለማስገባት በመስኖና ቆላ ሚኒስቴር ጥናት እንዲካሄድ መደረጉንም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በግድቡ ጉዳይ ላይ ሚኒስቴሩ እየሠራ ነው፤ አስጠግኖታል፤ ወደ አራት ኪሎ ሜትር የመስኖ ቦይ /ካናል/ ተሠርቷል ፡፡ በዚህ ዓመት ወደ 10 ሺህ 040 ሄክታር መሬት በማህበረሰቡና በኢንቨስትመንት በመስኖ በሚለማበት ሁኔታ ላይ ጥናት ተደርጓል፡፡

‹‹በዚህ ዓመት ትልቅ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራው ከዓሳ ምርት በተጨማሪ ሰፋፊ እርሻዎች በአርሶ አደሮች ሊሠሩ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ይደረጋል ፤ ግድቡ እስከ አሁን ባክኗል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You