ለቀጣይ ፖለቲካዊ ግንኙነት መሠረት የሚጥለው የአንካራው ስምምነት

ከሰሞኑ በቱርክ አንካራ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድ ስምምነት አድርገዋል፡፡ የሁለቱንም ሀገራት በሚጠቅሙ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረው የአንካራው ስምምነት፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እርስ በእርስ በመተባበር እና በመከባበር አንዱ የሌላውን ሉዓላዊነት እና ጥቅም በማክበር ለመንቀሳቀስ መግባባታቸውን የሚያመለክት ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በስምምነቱ ላይ ኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎቷ እንዲሟላ ሶማሊያም ተነሳሽነት እንዳላት ከመጠቆም ባሻገር፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ ለከፈለው መስዋዕትነት ሶማሊያ እውቅና እንደምትሰጥም ተገልጿል። ይህ ስምምነት አንድምታው እና ጠቀሜታው ምንድን ነው? ስንል ለፖለቲካ ምሁራን ላቀረብነው ጥያቄ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ በፍቃዱ ቦጋለ (ፕ/ር) በሰጡት ምላሽ፤ በቅድሚያ ስምምነቱ በቀጣናው ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ክስተት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በፍቃዱ (ፕ/ሮ) እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት የባህር በርን በተመለከተ ያስቀመጠችውን አቅጣጫ ለማሳካት ለጀመረችው ጥረት ዲፕሎማሲያዊ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሃሳቡን ስትገልፅ በጉልበት ሀገራትን ለመውረር ሳይሆን፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር ፍላጎቷን እንደምታሟላ ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ ጠቁማ ነበር፡፡ ስምምነቱ በተጨባጭ የጠቆመችውን እንደምትተገብር የሚያሳይ ነው፡፡

ስምምነቱ እንደሀገር የተቀመጠው የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን እያገኘ እንደሆነ የሚያሳይ መሆኑን ከማሳየት በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያ እውነትም በሰላማዊ መንገድ ዲፕሎማሲያዊ ጥቅሟን ለማስከበር ከሁሉም ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆኗን በተጨባጭ ያሳየችበት መሆኑንም አስረድተዋል።

ቀድማ ኢትዮጵያ የገለፀችው፤ እንዳለፉት ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ያለባህር በር ታፍና መቆየት አትችልም፡፡ ይህንን ደግሞ ጎረቤት ሀገሮች መረዳት አለባቸው በሚል ሃሳብ ስትሰነዝር ቅሬታዎች ነበሩ። አሁን ግን ስምምነቱ እንደሚያሳየው ሃሳቧ ትክክለኛ በመሆኑ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

እንደ በፍቃዱ (ፕ/ሮ) ገለፃ፤ የስምምነቱ ሰነድ ላይ የተቀመጡ ቃላቶች ኢትዮጵያ ዘላቂ፣ የተረጋገጠ፣ አስተማማኝ፣ ከባህር እና ወደ ባህር የሚወስድ መንገድ እንደሚያስፈልጋት እና እንደሚገባት ይህንን ሶማሊያም ሆነች አሸማጋይዋ ቱርክም እንደሚረዱ ይጠቁማል፡፡

ስምምነቱ ላይ በመቆም ከሶማሊያም ሆነ ከሌሎች ጎረቤት ሀገሮች ጋር ሥራዎችን ለመሥራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር የጠቆሙት በፍቃዱ (ፕ/ሮ)፤ ከዛ ባሻገር የኢትዮጵያን ፍላጎት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማሟላት በሚደረገው ጥረት ጎረቤቶች የመተባበር ሃላፊነት ፤ እንደቱርክ ያሉ ሀገራት ደግሞ የማሳለጥ ሃላፊነትን የሚጥል ስለሆነ በብዙ መልኩ ለኢትዮጵያ ጥቅም እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተም ስምምነቱ የሚኖረውን አውንታዊ ሚና ያስረዱት በፍቃዱ (ፕ/ሮ) ፤ ቀደም ሲል በሶማሊያ በኩል የከረሩ እና ፀረ ኢትዮጵያ ድርጊቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ለሶማሊያ ሰላም ስትከፍል የነበረውን ዋጋ እና መስዋትነት በመዘንጋት የተለያዩ ሃሳቦች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል። በቀጣይ ሰላም ማስከበር ኢትዮጵያ እንዳትሳተፍ፤ በኢትዮጵያ ምክንያት ፀረ አልሸባብ ውጊያው ወደ ኋላ እየተጎተተ ነው፤ የሚሉ እና ከሶማሌላንድ ጋር

የተፈረመው ስምምነት ካልቀረ ንግግር ብሎ ነገር የለም በማለት የማጥላላት አቋሞች ታይተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህኛው ስምምነት ከሶማሌላንድ ጋር ኢትዮጵያ ያካሔደችው ስምምነት አልተነሳም፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም እና ደህንነት ላበረከተችው አስተዋፅኦ እውቅና ይሰጣል፡፡ ቀጣይ በእዚህ ወር መጨረሻ ሶማሊያ ውስጥ የሚሰማራው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ሃይል ከኢትዮጵያ ውጪ የማድረግ መሠረት አይኖርም ማለት ነው ብለዋል፡፡

በፍቃዱ (ፕ/ሮ) እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን በኢትዮጵያ ሲረዱ ስለነበር በማመስገናቸው በቀጣይ ድጋፉን አንፈልግም የሚሉበት መሠረት አይኖርም፡፡

ከግብፅ አንፃር ሲደረጉ የነበሩ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ስምምነት በመፈረምም ሆነ ወታደር ለመላክ የነበሩ ጥረቶች እንደታሰበው ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ የመክተት ፍላጎቶች ፍሬ እንዳላፈሩ ስምምነቱ የሚያሳይ ነው፡፡

እንደቱርክ ያሉ ሀገራት የኢትዮጵያን ሰላማዊ ፍላጎት መረዳት፤ ለቀጣናው ሰላምና ትስስር ቁልፍ እንደሆነ የተረዱበትና ይህንንም ለማገዝ በሃላፊነት በመንቀሳቀስ ርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆኑ የሚያመላክት ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ስምምነቱ ለቀጣይ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ትልቅ መሠረት እንደሚጥል አስገንዝበዋል፡፡ አክለውም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተካሔደው ስምምነት ከኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በተጨማሪ ለቀጣናዊ ትስስር አስተዋፅኦ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች መሰረት እንደሌላቸውና በዘላቂነት ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ሊያመጡ እንደማይችሉ የሚያሳይ መሆኑን በመጠቆም፤ በተለይ የግብፅ እንቅስቃሴ ስኬታማ እንደማይሆን ያሳየ ነው ሲሉ ስምምነቱን በተመለከተ ያላቸውን ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፀሃፊ እና የፖለቲካ ባለሙያ አቶ ደስታ ዲንቃ እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ ከሶማሊያ ጋር የነበረውን ውጥረት የሚያረግብ እና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ አካሄድን የተከተለ በመሆኑ በማንም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡

ሶማሊያዎችም ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን ማንሳቷን ተገቢ ነው ብለው በመቀበላቸው፤ ውጥረቶችን ለማርገብ የሚያግዝ በመሆኑ ቱርክዬዎችም ይህንን ስምምነቱን በማዘጋጀታቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በስምምነቱ ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ እንደሚቋቋም መግባባት ላይ መደረሱ፤ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የባህር በር የመጠቀም ዕድሏ በአንድ ደረጃ ከፍ ማለቱ ለሀገሪቷ ከፍተኛ ጥቅም የሚስገኝ ነው ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ባለሙያው ደጉ አስረስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ምላሽ ሲሰጡ፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ ተግባብተው በሶማሊያ ወደቦች የመጠቀም ዕድል ይከፍታል፡፡ ይህንን ሶማሊያም ለራሷ ስትል የምታመቻቸው ነው፡፡ ምክንያቷ ደግሞ ኢትዮጵያ የባህር በር ስትጠቀም ትከፍላለች፤ ስምምነቱ ለሶማሊያም ሆነ ለኢትዮጵያ ለሁለቱም ጥቅም ያለው ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ አስገድዳ መጠቀም አትችልም፡፡ ነገር ግን በሰላማዊ መንገድ የመጠቀም ዕድል አላት፡፡›› የሚሉት ደጉ (ዶ/ር)፤ ከሶማሊያ ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ከኤርትራ ጋር በምፅዋ በኩል፤ ከሱዳኖች ጋርም ራሳቸው ኢትዮጵያን ፖርት ብለው እየተዘጋጁ ነበር፡፡ የሀገሮች ሉዓዋላዊ ግዛት በመሆኑ አለመግባባት ሲኖር ይቋረጣል። በሰላም ከሆነ ግን ኢትዮጵያ ያለምንም ችግር በተለያየ መልኩ የባህር በርን መጠቀም ትችላለች ብለዋል፡፡

ከጎረቤት ጋር ሰላም ሲሆኑ፤ ሰጥቶ የመቀበል ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡ ሲጣሉ መስጠትም መቀበልም ይቀራል። ያለው ግንኙነት ሰላም ከሆነ፤ ቀጣናውም ሰላም ይሆናል። ለሀገር ውስጥ ሰላምም የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲዳሰስ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ስምምነት በማንም ዘንድ መልካም የሚባል መሆኑን አመላክተዋል፡፡

እንደምሁራኑ ገለፃ፤ ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለቀጣይ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው፡፡ ቀጣናው ላይ ከሚኖረው በጎ ተፅዕኖ ባሻገር ለኢትዮጵያ የባህር በር የመጠቀም ዕድሏን የሚያሰፋላት እና እየሄደችበት ያለው የዲፕሎማሲ መንገድ ሰላማዊ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You