አዲስ አበባ፡- ከሜጋ ፕሮጀክቶች በተጓዳኝ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሸኽ መሀመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ድጋፍ የተገነባውን የኦሮሚያ አብዲ ቦሩ የህጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ትናንት መርቀው ከፍተዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ ወላጆቻቸውን ላጡና በችግር ውስጥ ያሉ ህጻናትን ተቀብሎ የሚያሳድግ ሲሆን፤ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችም የተሟሉለት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ የልማት ሥራዎቻችን የተሟሉ የሚሆኑት በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን ታሳቢ ሲያደርጉ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ እየተገነቡ ካሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተጓዳኝ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ወገኖችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡ ለአብነትም ማዕድ ማጋራት፤ የአቅመ ደካማና አረጋውያን ዜጎችን ቤት ማደስ፤ ለአይነ ስውራን የሚውል ትምህርት ቤት ግንባታና ሌሎች መሰል የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።
ለምርቃ የበቃው የህጻናት ማሳደጊያ ማዕከልም በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን የመደገፍ ሥራ አካል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሸኽ መሀመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ማሳደጊያ ማዕከሉን በመገንባት ረገድ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ላይ ድጋፍ እያደረጉ ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ ለዚህ በጎ ሥራም ትልቅ ክብርና ምስጋና እንሰጣለን ብለዋል።
በቀጣይም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በየአካባቢው የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችም አቅመ ደካማ ወገኖችን ታሳቢ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም