አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የወደፊቱን ታሳቢ በማድረግ ፈጣን የሠብዓዊ ድጋፍ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት የማኅበሩ የበላይ ጠባቂና የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ አሳሰቡ፡፡ ማህበሩ ባለፉት አራት ዓመታት ዓመታዊ ገቢውን ከ750 ሚሊዮን ወደ ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ማሳደጉ ተጠቆመ፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር 20ኛው ብሔራዊ ጠቅላላ ጉባዔ ትናንት ሲካሄድ ባደረጉት ንግግር፤ ላለፉት 90 ዓመታት ለሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ማኅበሩ የሰጠው ሠብዓዊ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ማኅበሩ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት የሚያስችለው ቁመና በሂደት መገንባቱን ገልጸው፤ የቀጣዩንም ታሳቢ በማድረግ ፈጣን የሠብዓዊ ድጋፍ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡
በሀገሪቱ ለተከሰቱ ድርቅ፣ ግጭት፣ የመሬት መንሸራተትና መሰል ችግሮች በተከሰቱበት ወቅት ለተጎዱ ወገኖች ያደረሰው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ በተለይም በሱዳን ባጋጠመው የርስ በርዕስ ግጭት በኢትዮጵያ ለተጠለሉ ሱዳናውያን ያደረገው ድጋፍ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑ ገልጸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ሠብዓዊ አገልግሎቶች ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ፈጣን ድጋፍና እገዛ በማድረግም ኃላፊነቱን የመወጣት ጥረቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ በበኩላቸው፤ በተለያዩ ምክንያቶች ተጎጂ ለሚሆኑ ሰዎች የሕይወት አድን ሥራ ከማከናወን በተጨማሪ ዘርፈ-ብዙ ሠብዓዊ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ያለፉት ሦስት ዓመታት የማኅበሩ ዓመታዊ ገቢ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ለ16 ሚሊዮን ሰዎች በድንገተኛ አደጋ ምላሽ እንዲሁም በአደጋ ሥጋት ቅነሳና መልሶ ማቋቋም ሥራ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል። መንግሥት ለማኅበሩ በየዓመቱ ሲያደርግ የነበረውን የ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ወደ 10 ሚሊዮን ብር ማሳደጉንም ጠቅሰዋል።
አቶ አበራ ቶላ እንደገለጹት፤ ማህበሩ ላለፉት 90 ዓመታት ሠብዓዊ ድጋፎችን፣ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ እንዲሁም በአደጋ ሥጋት ቅነሳና መልሶ የማቋቋም ሥራ በማከናወን በርካታ ወገኖችን ደግፏል ብለዋል።
አቶ አበራ ማህበሩ ባለፉት አራት ዓመታት ዓመታዊ ገቢውን 750 ሚሊዮን ብር ወደ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በማሳደግ ለ16 ሚሊዮን ሰዎች በድንገተኛ አደጋ ምላሽ እንዲሁም በአደጋ ስጋት ቅነሳ መልሶ ማማቋቋም ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በሚገኙት ከ80 በላይ መድኃኒት መደብሮቹ አማካኝነት በዓመት ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተመጣጣኝ ዋጋ የመድኃኒት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የማህበሩ በጎ ፍቃደኞች ቁጥር ስድስት ሚሊዮን መድረሱ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ፤ በቀጣይም በመላ ሀገሪቱ ይህንን ቁጥር ከፍ ለማድረግ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
አቶ አበራ ከውጭ የሚገኝ ርዳታ በቀነሰበት በዚህ ወቅት ማህበሩ በውጭ ድጋፍ ላይ የሚያደርገውን ጥገኝነት በመቀነስ በገቢ ራሱን ለመቻል ሰፊ የሀብት መሰባሰብ እና የማልማት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም