ቅዳሜ ሐምሌ 21 ቀን 1943 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስራ አንደኛ አመት ቁጥር 14 እትም “የከተማ ወሬ” በሚል አምድ ስር የስድስት ወንጀለኞችን የፍርድ ሂደት አስነብቦ ነበር፡፡
የወንጀለኞች ፍርድ
1ኛ ጋሻው ገሰሰ ፣ 2ኛ ማሞ ተሰማ ፣ 3ኛ ወልዴ ኦዳ ፣ 4ኛ ገሳ ባቢሶ ፣ 5ኛ ዓለማየሁ ጌታሁን ፣ 6ኛ ዓለማየሁ ዋሚ የተባሉ በከተማው ውስጥ እየተዘዋወሩ የ58 ሰዎች ንብረት የዘረፉ ወንጀለኞች በፖሊስ ኃይል ተይዘው ይህንኑ ወንጀል መስራታቸውን ከማረጋገጣቸው በላይ በየመኖሪያ ቤታቸውና በተቀባዮቻቸው ዘንድም የብዙ ሰው ንብረት ስለተገኘባቸው ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበውም አንደኛና ሁለተኛ ወንጀለኞች አርባ አርባ ጅራፍ ተገርፈው አምስት አምስት ዓመት እንዲታሰሩ ፤ 3ኛ ፣ 4ኛ፣ 5ኛ ፣ 6ኛ ተከሳሾች ግን ሰላሳ ሰላሳ ጅራፍ እንዲገረፉና ሶስት ሶስት ዓመት እንዲታሰሩ ተፈርዶባቸው ነበር፡፡
ነገር ግን የሰሩት ስራ በጣም ከፍ ያለ በመሆኑ የወንጀለኛ ምርመራ ክፍል ይግባኙን ለጠቅላይ ንጉሰ ነገስት ፍርድ ቤት አቅርቦ ስለነበረ ፤ የጠቅላይ ንጉሰ ነገስት ፍርድ ቤትም ፍርዱን ለውጦ አንደኛውንና ሁለተኛውን ወንጀለኞች በሞት እንዲቀጡ ሲፈርድ ፤ በቀሩት ወንጀለኞች ላይ አርባ አርባ ጅራፍ ግርፋትና አምስት አምስት አመት እስራት ፈረደባቸው፡፡
በተሰጠውም ፍርድ መሰረት ሐምሌ 14 ቀን ባለፈው ቅዳሜ ከቀኑ አምስት ሰዓት ሲሆን በዋናው ገበያ ውስጥ 1ኛ ወልዴ ኦዳ 2ኛ ገሳ ባቢሶ የተባሉት ሁለቱ ወንጀለኞች አርባ አርባ ጅራፍ ተገረፉ፡፡ እንዲሁም 3ኛው ወንጀለኛ አለማየሁ ጌታሁን ሐኪም ስለቀነሰለት 30 ጅራፍ 4ኛው ወንጀለኛ ዓለማየሁ ዋሚ 25 ጅራፍ ተገርፈዋል፡፡
እነዚህ ወንጀለኞች ቅጣታቸውን ከተቀበሉ በኋላ “እኛን እያያችሁ ተቀጡ እንደዚሁም ያለጥፋት ተጠንቀቁ” እያሉ ጥፋታቸውን ራሳቸው ተናጋሪና መካሪ ሆነዋል፡፡ ለፍርድ አጋልጦ የጣላቸውም የራሳቸው ጥፋትና ኃጢያት ነው፡፡
እግዚአብሔር ሰውን ጥረህ ግረህ በላብህ ወዝ ብላ ብሎታል እንጂ ያልደከመበትን የሌላውን ሰው ንብረት ነጥቆና ቀምቶ እንዲበላ አላዘዘውም፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔርም ሆነ ከመንግስት የተሰጠውን ትዕዛዝ ተላልፈው የወንጀል ስራ ሲሰሩ መገኘት ራስን ለቅጣት አሳልፎ መስጠት መሆኑ የታወቀ ነውና ይህን ከመሰለው ወንጀልና መጥፎ ስራ ርቆ ሀሳብን ሁልጊዜ ወደ ጨዋነት ምግባር መምራት በዚህኛውም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ጠቃሚ የሆነ የሰብዓዊነት ተግባር ነው፡፡ ሰውነትን ለወንጀል ስራ ማስገዛት ግን የገዛ ራስን ለታላቅ ቅጣት አሳልፎ መስጠት መሆኑን በእነዚህ ወንጀለኞች እንረዳለን፡፡
********
ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 1934 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንደኛ ዓመት ቁጥር 5 እትም ደግሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው ለሚማሩ ተማሪዎች ተከታዩን ማስታወቂያ አስነብቧል፡፡
ማስታወቂያ
በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር የሚፈልጉ ልጆች ሁሉ ተማሪ ቤት ከመግባታቸው በፊት ጤናቸውን በሀኪም መመርምር ፈንጣጣ መከተብና ማናቸውንም የተማሪ ቤቱን ደንብ ፈጽመው በተማሪ ቤቱ መዝገብ እንዲጻፉ የሚያስፈልጋቸው ስለሆነ ይህንኑ ለመፈጸም ከሚመጣው ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 18 ቀን ድረስ ጧት ከ 3 ሰዓት እስከ 7 ሰዓት እንዲሁም ከ 9 እስከ 11 ሰዓት ከተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ድረስ እንዲሰበሰቡ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት የትምህርትና የጥበብ ሚኒስቴር ያስታውቃል፡፡
ጥቅምት 7 ቀን 1934 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ሀምሌ10/2011