‹‹መጽሐፍት በሁኔታዎች ውስጥ የማይናወጹ ታማኝ ወዳጆች ናቸው፤ ባንጽፋቸው እንኳን እናንብባቸው›› የዝዋይ ማረሚያ ቤት ታራሚዎች የጋራ መፈክር ናት። ሰዎች በሚሠሯቸው በጎ ተግባራት እንደሚሸለሙ ሁሉ ለሚያጠፏቸው ጥፋቶችም ኃላፊነት ወስደው መታረም የግድ ይላቸዋል። ይህንንም አብነት በማድረግ በመላው ዓለም ጥፋተኛ የተባሉ ዜጎች በሕግ ጥላ ስር ውለው እርምት ይወስዳሉ።
የማረሚያ ቤት ሕይወት ምን ይመስላል፣ ምንስ የተለየ የሕይወት ፍልስፍና አለ፣ እንዴትስ ታራሚዎች ታርመው በእውቀትና በክህሎት ጎልብተው መውጣት ይችላሉ ሲል ኢፕድ በማረሚያ ቤቱ በመገኘት ታራሚዎችና የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎችን አነጋግሯል።
ኪሩቤል ሰለሞን ይባላል። በዝዋይ ተሐድሶ ልማት ማረሚያ ቤት የሕግ ታራሚ ነው። ከዝዋይ በፊት በቂሊንጦና ቃሊቲ ማረሚያ ቤቶች መቆየቱን ተናግሯል። በወንጀል ጥፋተኛ የተባለበትን በግል ጉዳይ ይፋ ማድረግ ባይፈልግም ከአምስት ዓመት ከስምንት ወር በፊት ነበር ጥፋተኛ ተብሎ ማረሚያ ቤት የገባው። አሁን ላይ 12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በዝዋይ ተሐድሶ ልማት ማረሚያ ቤት የብሩህ ተስፋ ኪነ ጥበብ ቡድን መሥራችና ጸሐፊ እንዲሁም ማረሚያ ቤቱ ለሚቀላቀሉ ታራሚዎች የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሙያዎች ላይ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።
በተጨማሪም በማረሚያ ቤቱ በትወና፣ በዳንስ፣ በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነትና አሠልጣኝነት እያገለገለም ነው።
መጽሐፍ ጓደኛ ነው፤ ማረሚያ ቤት ከመግባቴ በፊት የተወሰነ የማንበብ ልምድ ነበረኝ የሚለው ታራሚው፣ ይሁን እንጂ ማረሚያ ቤት ገብቼ የማንበብ ልምዴ ካዳበርኩ በኋላ የተሻለ የሕይወት እርምጃ እንድራመድ ረድቶኛል ይላል።
ማረሚያ ቤቶች የእውቀት አድማስ ማስፊያ፣ የስብዕና መገንቢያ፣ አመለካከትና እይታ ማስተካከያ እንዲሁም በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተቀመመ ክህሎት ማጎልበቻ ሲሆኑ ትውልድ አሻጋሪ የሆኑ ሃሳቦች መፍለቂያ ይሆናል ባይ ነው።
ከማንበብ በዘለለም በተለያዩ የቀለምና የክህሎት ሥልጠናዎች ላይ እየተካፈለ እንደሚገኝ ይጠቁማል።
በማረሚያ ቤት ቆይታው አንድ የግጥም መድብል ስምንት ያለቀላቸው እንዲሁም ስድስት በሂደት ላይ የሚገኙ የሙዚቃ ሥራዎች ማዘጋጀቱን ገልጾ፤ አሁን ላይ በማረሚያ ቤቱ ስፖርትና መዝናኛ፣ የቤተ መጽሐፍት አገልግሎት፣ የኪነ ጥበብ ሥልጠናዎች፣ የቀለም ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑ ይናገራል።
በማረሚያ ቤቶች የተለያዩ ሰዎች የሕይወት ውጣ ውረድ ልምድ እንዲሁም ውጤታማ ለመሆን ያደረጉትን ተጋድሎ በጥሞና የሚታይበት ነው። ይህም ስብዕናንና አመለካከትን ለመቅረጽ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ያነሳል።
እንደ ታራሚ ኪሩቤል ገለጻ፤ የሠራው ወንጀል ትክክል ባይሆንም እውነታውን አምኖ መቀበሉ ከአጉል ጸጸት ወጥቶ ለቀጣዩ ሕይወቱ አዲስ ምዕራፍ እንዲከፍት አስችሎታል። ሰዎች በቀድሞ ሥራቸው የቱንም ያህል ቢጸጸቱም ለጸጸታቸው መካሻ እንድ ዕድል ቢኖር እሱም አመለካከታቸውን፣ ስብዕናቸውን የተሻለ አድርገውና ክህሎታቸውን አጎልብተው ሀገራቸውን መካስ ብቻ ነው።
ሌላኛው ከኢፕድ ጋር ቆይታ ያደረገው የሕግ ታራሚ ዘላለም ገዛኸኝ ነው። ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በማረሚያ ቤት ላይ ቆይታ አድርጓል። የግጥም፣ የዜማና የመጽሐፍት ደራሲ እንዲሁም ሙዚቀኛ ነው። ማረሚያ ቤት መግባቴ የጥሞና ጊዜ እንድናገኝና ማንነቴን እንዳጤን ረድቶኛል የሚለው ታራሚው፤ ማረሚያ ቤት ከመግባቴ በፊት ስለ ሥነ-ፅሑፍም ሆነ ስለሙዚቃ ምንም ዝንባሌ እንዳልነበረው ይናገራል።
መጀመሪያ ስገባ ከፍተኛ ጭንቀት ነበረብኝ በኋላ እየቆየው ስሄድ ግን እራሴን እንዳውቅ ረድቶኛል ያለ ሲሆን ከ48 በላይ ግጥምና ዜማ እንዲሁም ሦስት መጽሕፍት መጻፉን ይገልጻል።
ማረሚያ ቤቱ የሕግ ታራሚዎች በእውቀት በክህሎትና በአስተሳሰብ ጎልብተው እንዲወጡ የተለያዩ የትምህርትና ሥልጠና ዘርፎች መርጦ እየሠራ ይገኛል ያሉት ደግሞ በዝዋይ ተሐድሶ ልማት ማረሚያ ቤት የትምህርትና ሥልጠና ቡድን መሪ ረዳት ኢንስፔክተር እንድሪስ አወል ናቸው።
ታራሚዎች ዓለም ከደረሰችበት እኩል እንዲጓዙ ቴክኖሎጂ ነክ ነገሮች፣ የተለያዩ የክህሎትና የሥነ-ልቦና ማጎልበቻ ሥልጠናዎች እንዲሁም ዘመኑን የዋጁና የተለያዩ አይነት ስብጥር ያላቸው መጽሐፍት በድጋፍ መልክ በማስገባት እውቀት እንዲሸምቱ እየተደረገ መሆኑን ያስረዳሉ።
በማረሚያ ቤቱ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸው ታራሚዎች በመለየት በየዘርፉ ተሰጥዖዋቸውን እንዲያጎለብቱ የድጋፍና ክትትል በተጨማሪ አንባቢ ትውልድ እንዲፈጠር እንደሀገር የተያዘውን ግብ ለማሳካት ትኩረት ተደርጓል።
ታራሚዎች በአጭር የእርምት ጊዜያቸው ትላልቅ ተግባራት ሲያከናውኑ ላጤነ ማረሚያ ቤት ለባከነ ሰዓት ማካካሻ ይሆን ወደሚል ድምዳሜ ሳይወስድ አይቀርም።
የሰው ልጅ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ወንጀል ይሠራል። ታዲያ በሕግ ጥላ ስር ሆኖ ወንጀሉን ማረሙ የግድ ይለዋል። ይሁን እንጂ በሠራው ወንጀል ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲገታ ከቤተሰብ ርቆና የሥነ ልቦና ጫና ተቋቁሞ ነገ የተሻለ ለማድረግ የሚጥር ዜጋ ሀገርንም አንድ እርምጃ የሚያራምድ ነው።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመንታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም