– የቀይ ባሕር የዲፕሎማቲክ የወጣቶች ጉባኤ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፡- የዓባይ ወንዝና የባሕር በር ለኢትዮጵያ የመደራደሪያና የማደጊያ አቅሞች መሆናቸውን የአፕሊፍት ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ መሥራችና ዳይሬክተር አቡበከር ሰማን አስታወቀ፡፡- የቀይ ባሕር የዲፕሎማቲክ የወጣቶች ጉባኤ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡
የአፕሊፍት ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ መሥራችና ዳይሬክተር አቡበከር ሰማን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ የትውልድ ጥያቄና በጋራ የመልማት አጀንዳ ነው።ከዚህ አኳያም የዓባይ ወንዝና የባሕር በር ለኢትዮጵያ የመደራደሪያና የማደጊያ አቅሞች ናቸው፡፡
አፕሊፍት ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በትምህርት፣ በሠላምና ደኅንነት ዙሪያ ወጣቶችን የማብቃት ሥራ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የወጪ ገቢ ንግድ በቀይ ባሕር ላይ ጥገኛ ነው።ቀይ ባሕር ላይ የሚከሰቱ ችግሮች ኢትዮጵያን በቀጥታ የሚነኩ በመሆናቸው ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ቀይ ባሕርን ማልማት፣ መጠቀምና መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የቀጣናው ወጣቶች ትልቅ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አመልክተው፤ በቀጣናው ሠላም እንዲመጣና የተረጋጋ ግንኙነት እንዲኖር የቀይ ባሕር ተጎራባች ሀገራት ወጣቶች ጋር መምከር ያስፈልጋል በሚል ዕሳቤም የቀይ ባሕር የዲፕሎማቲክ የወጣቶች ጉባኤ የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የዓባይ ወንዝና የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የመደራደሪያና የማደጊያ አቅሞች ናቸው።የባሕር በር መጠቀም ማለት በዓለም የንግድ ሥርዓት ውስጥ ሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ነው።ይህም በሀገር ውስጥ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ያስችላል።የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባትና ሠላም ማምጣት ካልቻሉ ቀጣናው ሙሉ ለሙሉ በኃያላን ሀገራት ቁጥጥር ስር ይወድቃል።
የባሕር በር በዓለም መድረክ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ አቅም ይፈጥራል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በሁለቱ ጉዳዮች ላይ በሚገባ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ከተቻለ ከየትኛውም ሀገር ጋር በሰጥቶ መቀበል መርሕ በሠላማዊ መንገድ የባሕር በር ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ገልጸዋል።
በስደት ወቅት የባሕር ሲሳይ የሚሆነውን ወጣት ቁጥር ለመቀነስ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በጋራ መሥራት አለባቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የቀጣናው ሀገራት ሀብቶችን በጋራ አልምተው ለጋራ እድገት ሊጠቀሙ ይገባል ነው ያሉት።
በቀጣናው በርካታ ኃያላን ሀገራት ወደብ አልምተውና የጦር ሰፈር ገንብተው የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም እያስጠበቁ ነው።ነገር ግን ኢትዮጵያም በቅርብ ርቀት ተቀምጣ፣ ሰፊ ኢኮኖሚና የሕዝብ ቁጥር ይዞ የቀይ ባሕር ተመልካች ሆና መቀጠል ስለማይቻል የባሕር በር ሊኖራት ይገባል ብለዋል፡፡
እንደ አቡበከር ማብራሪያ፤ የአፕሊፍት ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ በቅርቡ በቀጣናው ሠላም ዙሪያ የቀይ ባሕር የዲፕሎማቲክ የወጣቶች ጉባኤ ለማዘጋጀት በዝግጅት ላይ ይገኛል። በጉበኤው ላይ ከቀይ ባሕር አጎራባች ሀገራት የተውጣጡ ከ300 በላይ ወጣቶች የሚገኙ ሲሆን ዋና ዓላማ ወጣቶች አዲስ አበባ መጥተው ስለ ቀይ ባሕር የሚያወሩበትና የሚወያዩበት ነው። ጉባኤው ከመጋቢት 12 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ለሦስት ተከታተይ ቀናት ይካሄዳል፡፡
ቀይ ባሕር ሥነ ምድራዊ አቀማመጥ (ጂኦግራፊካል) ጠቀሜታ ትልቅነትና ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት እንደምትገኝ በመግለጽ፤ የባሕር በር ለማግኘት ያቀረበችው ጥያቄ ተገቢ ስለመሆኑ ለቀጣናው ሀገራት ወጣቶች ገለጻ እንደሚደረግም አስገዝበዋል። ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የከፈለችውን መስዋዕትነት፣ ለቀይ ባሕርም ሩቅ እንዳልሆነችና ያቀረበችው ጥያቄ ምክንያታዊ መሆኑን ለወጣቶች የማስረዳትና የማስገንዘብ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
ሞገስ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም