ፕሬዚዳንት አብዱራህማን በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል ያለውን አጋርነት እንደሚያከብሩ አስታወቁ

– ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት የምታደርገውን ጠንካራ ድጋፍ አደነቁ

ሐርጌሳ፡– አዲሱ የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት አብዱራህማን ሞሐመድ በመከባበር ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ አጋርነት እንደሚያከብሩ አስታወቁ። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት የምታደርገውን ጠንካራ ድጋፍ አደነቁ ።

ፕሬዚዳንት አብዱራህማን የራስ ገዟ ሶማሊላንድ 6ኛ ፕሬዚዳንት ሆነው ለመሥራት ከትናንት በስቲያ ቃለ መሓላ በፈጸሙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን በመከባበር ላይ የተመሠረተ አጋርነት እንዲሁም የጋራ፣ የሠላም እና የብልፅግና ጉዞ  ታከብራለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሠላምና ልማት ያላት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ስትራቴጂካዊ ጎረቤት እና ወሳኝ አጋር ናት፤ ከሷ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በልማት እና በሰብዓዊ ርምጃዎች ላደረገችው አስተዋፅዖ አድናቆታቸውን ገልፀው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ሀገራቸው በቀጣይ የድንበር ተሻጋሪ ንግድን፤ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በፀጥታ፣ በሥራ አጥነት እና በመሳሰሉ ቀጣናዊ ችግሮች ዙሪያ መሥራት ባቀደቻቸው ሥራዎች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ሙሑመድ ዑመር እና የኢፌዲሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በመርሐ-ግብሩ መገኘት በኢትዮጵያ እና የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት አጉልቶ የሚያሳይ እንደሆነም አመልክተዋል።

ፕሬዚዳንት አብዱራህማን ለሀገራዊ አንድነት፣ ለኢኮኖሚያዊ ልማትና ለቀጣናዊ ትብብር ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል።ጠንካራ፣ ሁሉንም ያካተተች ሶማሊላንድን ለመገንባት ጉዞ ጀምረናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የፖለቲካ ጉዳይ ምንም ይሁን ምን እያንዳንዱ ዜጋ ብሩህ ተስፋ እንዲኖረው በጋራ እንሠራለን ብለዋል።

የፕሬዚዳንት አብዱላሂ ሹመት በኅዳር 2024 በተካሄደው ምርጫ ወሳኝ ድል ማግኘቱን ተከትሎ ከ14 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ለሚረከበው የዋይታዲ ፓርቲ ታሪካዊ ቀን ነው። ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግሩ ለአፍሪካ ቀንድ የተስፋ ብርሃን ሆኖ የሚያገለግል እንደሆነም አስታውቀዋል ።

በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሐርጌሳ በተካሔደው የሥልጣን ርክክብ ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ሙሐመድ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ባሳለፍነው ኅዳር ወር በተካሄደው ሠላማዊ ምርጫ ፕሬዚዳንት አብዱራሃማን ሞሐመድ አብዱላሂ የመራጩን ድምፅ 64 በመቶ በማግኘት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ከሙሴ ቢሒ አብዲ ማሸነፋቸው ይታወሳል።

ሕዝቅኤል ኃይሉ

 

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You