አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለአምስት የመንግሥት ሆስፒታሎች 750 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ ። ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህን ፈለግ በመከተል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ ።
በኡስታዝ አቡበከር አሕመድ አስተባባሪነት ከሙስሊም ኤድ አሜሪካ የተገኘውን ድጋፍ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ትናንት ለሆስፒታሎቹ ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፉ መተጋገዝና መረዳዳት ከተቻለ ችግሮችን በቀላሉ መፍታት እንደሚቻል ማሳያ ነው። የአቅማችንን በማድረግ በመተጋገዝና በመረዳዳት ከሠራን ሀገርን መጥቀምና የሰዎችን ችግር ማቃለል እንችላለን ብለዋል።
በጤና ሚኒስቴር የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ማብራቱ ማሴቦ በበኩላቸው፤ መንግሥት ብቻውን የጤና አገልግሎትን ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ እንደማይችል ገልጸው፤ የተደረገው ድጋፍ የጤና አገልግሎቶትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አስታውቀዋል። የዜጎችን የጤና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የመሰል ተቋማት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። ድጋፉ በተለይ ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን ጫና እንደሚያቃልል ጠቁመዋል።
በጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዑስታዝ አቡበከር አሕመድ በበኩላቸው፤ በሙስሊም ኤይድ ዩ.ኤስ.ኤ የተደረገው ድጋፍ እንደ ሀገር በሆስፒታሎች የሚታየውን የሕክምና ግብዓት እጥረት ለመፍታት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
በሙስሊም ኤይድ ዩ.ኤስ.ኤ የተደረገው የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች ድጋፍ ግምታዊ ዋጋቸው 750 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን ገልጠው፣ ጥራታቸው በዓለም ጤና ድርጅት የተረጋገጡ እና የአውሮፓን ደረጃን (ስታንዳርድ) ያሟሉ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ሙስሊሙ ኤድ አሜሪካ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ግምቱ 15 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የሕክምና መድኃኒቶችንና ግብዓቶችን መለገሳቸውን አውስተው፤ የዛሬው ድጋፉ ለሰባተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል። ድጋፉ በቀጣይ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል። ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህን ፈለግ በመከተል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በትራንዚት መዘግየት ምክንያት በጅቡቲ ወደብ ላይ አምስት ኮንቴነር መድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶች መኖራቸውን የገለጹት ዑስታዝ አቡበከር፤ ቁሳቁሶቹ ወደ ሀገር ሲገቡ ለተቀሩ አካባቢዎች እንደሚከፋፈል ተናግረዋል። በቀጣይም ምክር ቤቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለማኅበረሰብ የሚጠቅሙ ግብዓቶችን የማፈላለግ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በሙስሊም ኤይድ ዩ.ኤስ.ኤ ግብረ ሰናይ ድርጅት ላደረገው ድጋፍ እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እንዲሁም የጉምሩክ ኮሚሽን ከውጭ የመጡት ቁሳቁሶቹ በአጭር ጊዜ እንዲደርሱ በማድረግ በኩል ላደረጉት አስተዋፅዖ በምክር ቤቱ ምስጋና አቅርበዋል።
ድጋፉ የተደረገው ለድል ጮራ፣ ለአሶሳ፣ ጅግጅጋ ሆስፒታሎች፣ ለሙሑር አክሊል የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና ለስልጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሲሆኑ፣ በእለቱም ጠቅላይ ምክር ቤቱ የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶቹ ሀገር ቤት እንዲገቡ አስተዋፅዖ ላበረከቱ መንግሥታዊ ተቋማትና ግለሰቦች ሽልማት አበርክቷል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም