ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ጀርባ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከሰሞኑን የተመሠረተበትንና የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ማቋቋሚያ ስምምነት የተፈረመበት 80ኛ ዓመት በዓል እያከበረ ነው። በክብረ በዓሉ የተገኙት የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ጄኔራል ሉሲ ዋንጂኩ ምቡጓ፣ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ የሚተማመኑበትና ዘመናዊነትን የተከተለ ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አቪዬሽን ውስጥ ባላት የመሪነት ሚና ኩራት እንደሚሰማቸውም ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ሲቪል የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው እያደገና እየዘመነ መምጣት አሁን ላለው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ወሳኝ ነው ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ባይኖር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይኖራል ብሎ ማሰብ እንደማይቻልም ያነሳሉ። በእርግጥ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተከታታይ ሽልማትም ሆነ ስመ ገናናነት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ሚና ምንድን ነው? ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች ጠይቀናል።

የአቪዬሽን ጸሐፊው (የበረራ ባለሙያ) አቶ ዮናታን መንክር ካሣ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተመሠረተው ከዛሬ ስምንት አስርት ዓመት በፊት ነው። ይህንኑ አስመልክቶ ከሰሞኑን 80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ እያከበረ ይገኛል። ባለሥልጣኑ ይህን በዓል የሚያከበረው የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (In­ternational Civil Aviation Organization (ICAO) ጋር እኩል ነው። ምክንያቱም የተቋቋምነው በአንድ ጊዜ ነው።

የዛሬ 80 ዓመት በአሜሪካ ቺካጎ ውስጥ በተካሔደ ኮንቬንሽን ላይ የተሳተፉት 52 ሀገራት ብቻ ናቸው የሚሉት ባለሙያው ዮናታን፣ በወቅቱ ብቁ ናቸው የተባሉት እነዚያ 52 ሀገራት ተሰብስበው የዓለም አቀፉን የሲቪል አቪዬሽንን ድርጅት መመሥረታቸውን ያስረዳሉ። የመሠረቱት ተቋም የተባበሩት መንግሥታት በአቪዬሽን መስክ ላለው አንድ ክፍል ነው ይላሉ።

አቪዬሽንን የሚመለከት በረራዎች፣ ደኅንነቶች፣ የአቪዬሽን ልማቶችና የመሳሰሉት በሙሉ በዚህ ተቋም ውስጥ የሚከናወኑ መሆናቸውንም ያመለክታሉ።

የዛሬ 80 ዓመት አፍሪካ የት ነበረች? ብለን ስናስብ ኢትዮጵያ በዚያን ጊዜ አሜሪካ ቺካጎ ሔዳ በወቅቱ ከነበሩ ያደጉ ሀገራት ጋር እኩል ድምፅ ሰጥታ መሥራች መሆኗ ለአሁኑ ጥንካሬዋ ቀድማ መሠረት የጣለች መሆኑን ያመላክታል። የዚያን ጊዜ እንቅስቃሴዋ አመላካችነቱ የኢትዮጵያን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን አቪዬሽን ለሚባለው ቴክኖሎጂ የሰጠችውን ዋጋና ትኩረት ነው ሲሉ ዮናታን ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ የዚያን ጊዜ ተግባር ነገ እዚህ ይደርሳል ብላ የተለመችበትን ትልቅ ሕልም አመላካች እንደሆነም ያብራራሉ።

ይህ ምን ማለት እንደሆነ የሚተነትኑት የአቪዬሽን ጸሐፊው ዮናታን፣ ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ቁመና በአፍሪካ አንደኛው አየር መንገድ እንዲሁም በዓለም አቀፍም በጣም ተወዳዳሪ አየር መንገድ ሆኖ እንዲቀጥል ያስቻለው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን መኖሩ ነው ይላሉ። ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሱት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አድማሶቹን አሰፋ ስንል በራሱ ከመንግሥታት ጋር ተዋዋለ፤ ተነጋገረ ማለት አይደለም ይላሉ። ከመንግሥታት ጋር የሚዋዋለውም ሆነ የሚነጋገረው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ነው። ከሀገራት ጋር ይነጋገራል፤ መስመሮችን እንዲከፍቱ ያደርጋል ሲሉ ያስረዳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ለአየር መንገዱ ያለው ሚና የሚገለጸው በተለያየ መንገድ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ወደ የሀገራቱ እንዲበሩ የሚደረገው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ያለው ደኅንነትንና የመቆጣጠር አቅም ታይቶ ነው። በመሆኑም ይህ ሲታሰብ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ባይኖር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ትራንስፖርት ፋይዳው ከፍ ያለና ለኢኮኖሚው እድገት ቁልፍ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከ112 ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ የአየር አገልግሎት ስምምነቶችን ተፈራርሟል። የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የሚደግፍ ወሳኝ የቁጥጥር ማሕቀፍም አዘጋጅቷል።

ሚኒስትሩ ዓለሙ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የአየር ትራንስፖርትን ለማስተዋወቅ ከዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት እና ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር በቅርበት ለመሥራት ቁርጠኛ ነች። ኢትዮጵያ የሚያጋጥማትን ፈተናዎች ለማሸነፍ ዓለም አቀፍ ትብብር ቁልፍ ነው ብላ የምታምን ሀገር ነች።

ሚኒስትሩ፣ ልክ እንደ አቪዬሽን ባለሙያው ዮናታን ሁሉ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው እያደገ መሔድ አሁን ላለው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ወሳኝ ነው ይላሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብሔራዊ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እድገትና ምኞት ምልክት ጭምር እንደሆነም ያመለክታሉ።

በአሕጉሪቱ ሰፊ ትስስር ያለው እና ለአፍሪካ ልማት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ጠንካራ ቁርጠኝነት ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እውነተኛ የመላ አፍሪካ አየር መንገድ ነው። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ደግሞ ለአየር መንገዱ ማስፋፊያ አስፈላጊ የሆነውን በክልላዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስፈላጊውን የቁጥጥር ድጋፍ በማድረግ የእድገት መሠረት ሆኖ መቆየቱንም ዓለሙ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ የቢዝነስ ተቋም ነው የሚሉት ደግሞ የአቪዬሽን ጸሐፊው ዮናታን፣ ለእኛ ግን ከቢዝነስ ተቋም ባለፈ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችንን አንግቦ ከአሕጉር አሕጉር የሚዘዋወር አየር መንገዳችን ነው በማለት ኢትዮጵያን የሚያስጠራ ተቋም መሆኑን ይናገራሉ። አየር መንገዱ፣ ተወዳዳሪ እንዲሆን፣ ትርፋማ እንዲሆን እንዲሁም ዘለቄታ እንዲኖረው እና እያደገ እንዲሔድ ደግሞ ባለሥልጣኑ ድርሻው ጉልህ እንደሆነ ያስረዳሉ፡

የአቪዬሽን ጸሐፊው እንደሚናገሩት ከሆነ፤ አቪዬሽኑ ለሀገር የሚሰጠው ፋይዳ ትልቅ ነው። በመጀመሪያ ሀገር በብዙ መንገድ ይገለጻል። እኛ በአቪዬሽን ዘርፍ ላሉ ጉዳዮቻችን ሌሎች ሀገራት የሚያውቁን በዋነኝነት ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የምንፈጥረው በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አማካይነት ነው። ባለሥልጣኑ ይህን የሚያደርገው አየር መንገዶች ለብቻቸው ሔደው ከሀገራት ጋር ግንኙነት ስለማይፈጽሙ ነው። ጠንካራ ሲቪል አቪዬሽን አለ ማለት በሌሎች ሀገራት የሚከበር አየር መንገድ እንዲኖረን ብሎም የሚከበር የአቪዬሽን ተቋም እንዲኖር ያስችላል ማለት ነው ብለዋል።

ሲቪል አቪዬሽን በዋናነት ለአየር መንገዱ ያለው አገልግሎት አንደኛ የመቆጣጠር ሥራ መሥራቱ ነው። በጠቅላላ ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው አስፈላጊ የሚባሉትን ፖሊሲዎችን፣ ሕጎችን፣ መመሪያዎችንና ደንቦችን፤ የሚያወጣው፣ የሚያስፈጽመውና የሚቆጣጠር አካል ነው። ሁለተኛው ተግባሩ ለባለሙያዎች ፈቃድ መስጠት ነው። አብራሪዎች ወይም የአቪዬሽን ባለሙያዎች ፈቃድ የሚያገኙት ከዚህ ተቋም ነው። ሦስተኛ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር አገልግሎት ነው።

የአቪዬሽን ጸሐፊው፣ በኢትዮጵያ ሰማይ የሚበር ማንኛውም አውሮፕላን የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር አውሮፕላን ፈቃድ የሚያገኘው፣ መመሪያ፣ አቅጣጫ ወይም ደግሞ መረጃ የሚያገኘው ከዚህ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪው ዘምኗል ሊባል የሚችል ነው፤ ለዚህ አንዱ መገለጫው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማነት ነው። በጣም ዘመናዊ የሆኑ አውሮፕላኖችን በዓለም ሲመረቱ ቀድመው ከሚያስገቡ ጥቂት አየር መንገዶች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው ያሉት የአቪዬሽን ጸሐፊው ዮናታን፣ አየር መንገዱ ብዙ መዳረሻዎች ያሉት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በገበያ ጥናትና በራሱ ምርጫ ካልሆነ በስተቀር በደኅንነት ስጋት የተከለከለበት ሀገርም እንደሌለም ተናግረዋል። እንዲህ ማለት ደግሞ እሥራኤልን ወይም አሜሪካንን አሊያም ደግሞ አውሮፓን ብንወስድ ከፍተኛ የበረራ ደኅንነት ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሀገራት ናቸው ሲሉ ጠቅሰው፤ የእነዚህን መስፈርቶች በማሟላት በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ የሚጠበቅበት ዘመናዊነትን አሟልቷል ማለት ነው ሲሉ አብራርተዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከዛሬ 80 ዓመት በፊት እኤአ ታኅሣሥ 7 ቀን 1944 በአሜሪካ ቺካጎ ከተማ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት በ52 ሀገራት ሲመሠረት ከአፍሪካ ሦስት መሥራች ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች ይታወሳል። ከድርጅቱ ምሥረታ በኋላ በቀናት ልዩነት ታኅሣሥ 12 ቀን 1937 ዓ.ም “የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን አገልግሎት” በሚል ስያሜ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን አገልግሎት በአዋጅ መቋቋሙ የሚታወስ ነው። አገልግሎቱ በተቋቋመ በዓመቱ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው እና በዓለም አቀፍም ተወዳዳሪነቱን እያስመሰከረ የመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መቋቋሙም የሚታወቅ መሆኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፤ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀርባ አጥንት ሆኖ የሚቀጥል ከመሆኑም በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ባሕል፣ ቱሪዝም፣ ንግድና ኢንዱስትሪ እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You